የህዳሴ ግድብን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የምሁራን ሚና ወሳኝ ነው-- የሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የምሁራን ሚና ወሳኝ ነው-- የሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር
ፍቼ ግንቦት 28/2013/ኢዜአ/ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ምሁራን የህዳሴ ግድብን ዘለቄታዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ ሊሰሩ እንደሚገባ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስገነዘበ።
"የበረሀ ቀርቀሀ በማልማትና የአባይ ተፋሰስን በመጠበቅ የህዳሴ ግድብ ዘላቂ ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን" በሚል መሪ ሀሳብ የሰላሌ ዩኒቨርስቲ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተዘጋጀ ሀገር አቀፍ የምሁራን ውይይት በፍቼ ከተማ ተካሂዷል።
በወይይቱ መክፈቻ ላይ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ምሁራን የህዳሴ ግድብ ለፍፃሜ እስኪደርሰ ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ በግድቡ ዙሪያ የተቀናጀ የልማት ስራ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል።
በተለይም ግድቡ ለፍፃሜ ከመድረሱ በፊት በደለል እንይሞላና አፈሩ እንዳሸረሸር የሚረዱ የተግባር ሥራዎችን ህብረተሰብን ባሳተፈ መልክ ማከናወን ከምሁራኑ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል።
ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ መሠረት የሚጥል መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው ይህንን ታሳቢ ያደረገ የምሁራን አንድነትና እውቀት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ግድቡ በህዝብ ትብብርና ድጋፍ ሊጠናቀቅ 20 በመቶ የሚሆን ስራ እንደቀሩት የጠቆሙት የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማሰተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ታገል ቀኑብህ ይህን ውጤት ምሁራን ይበልጥ ሊያጎለብቱትና ሊያጠናክሩት የሚገባም ጠቁመዋል።
ባለፋት 10 ወራት ብቻ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለግድቡ ግንባታ ባደረገው ድጋፍ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ በቦንድና በጥሬ ገንዘብ መሰብሰቡን ገልጸዋል።
የአባይን ተፋሰስ ጨምሮ በመላ ሐገሪቱ የአካባቢውን የአየር ሁኔታና ስነ-ምህዳር ለመጠበቅ የአረንጓዴ ልማት ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የአባይ ተፋሰስ በሚያልፍባቸው ወረ ጃርሶና ደጀን ወረዳ ሐገር በቀል ችግኞችን በማልማት አካባቢውን በደን ለመሸፈን እየሰራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ገናናው ጎፌ ተናግረዋል።
በዚህም አንድ ሚሊዮን የሚሆን ሐገር በቀል የቀርከሀ ችግኞችን በማፍላት ከ800 ሄክታር የሚበልጥ መሬት ለመሸፈን ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ትላንት በተካሔደው በዚህ ውይይት ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ከሰላሌ ዩኒቨርሲቲ፣ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤትና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ ተሳታፊዎች በውይይቱ ተገኝተዋል።