በኢፌዲሪ አየር ኃይል የምስራቅ አየር ኃይል ምድብ ለሠራዊቱ የዕውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር አካሔደ - ኢዜአ አማርኛ
በኢፌዲሪ አየር ኃይል የምስራቅ አየር ኃይል ምድብ ለሠራዊቱ የዕውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር አካሔደ
ድሬዳዋ ግንቦት 28/2013 (ኢዜአ) በአለም አቀፍ ሰላም እና በአገር ውስጥ ህግ ማስከበር ተልዕኮ ኃላፊነታቸውን ለተወጡ በኢፌዲሪ አየር ኃይል አባላትና ተቋማት ዕውቅናና ሽልማት ተበረከተ::
በዕለቱ ሽልማቱን የሰጡት በኢፌዲሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ይልማ መርዳሳና የምስራቅ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ኮሮኔል አበበ ለገሰ ናቸው።
የምስራቅ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ኮሎኔል አበበ ለገሰ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት አየር ኃይል በአገሪቱ የሚቃጡ ማናቸውንም ትንኮሳዎች በመመከት የአገሪቱን ሉአላዊነት ለመጠበቅ ከምንግዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል ።
“ህግን የማስከበሩን ተግባር በማጠናከር በአገሪቱ የተጀመሩ ሁሉን አቀፍ የሰላምና የልማት ተግባራት እንዲጠናከሩ ተግቶ ይሰራል” ብለዋል።
በኢፌዲሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው ለተቋማት የተዘጋጀውን የምስክር ወረቀት የላቀ ተልዕኮ ለፈፀሙት ደግሞ የማዕረግ እና የገንዘብ ሽልማትን አበርክተዋል ።
በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክትም “ሠራዊቱ ከምንግዜውም በላይ አንድነቱን አጠናክሮ ግዳጁን እየተወጣ ይገኛል” ብለዋል።
“በውስጥም ሆነ በውጭ ቀጣዩን ምርጫ ተገን በማድረግ አገሪቱን ለማተራመስ እና ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚከናወኑ ተግባራት መቼም ቢሆን አይሳኩም” ብለዋል።
“የአገሪቱ ሉአላዊነት መገለጫ የሆነው ሠራዊት የህዳሴውን ግድብ እንደ አይኑ ብሌን በመጠበቅ ላይ መሆኑን ገልጸው የውሃ ሙሌቱ በተቀመጠው ጊዜ እንዲፈፀም የሚጠበቅበትን እየሰራ መሆኑንም ሜጄር ጀነራል ይልማ መርዳሳ አስረድተዋል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድና የካቢኔ አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።