የሀገሪቱ የደን ሽፋን 17 ነጥብ 5 በመቶ ደረሰ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገሪቱ የደን ሽፋን 17 ነጥብ 5 በመቶ ደረሰ
ሀዋሳ፤ ግንቦት 28/ 2013(ኢዜአ) ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወነ የችግኝ ተከላና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ የሀገሪቱ የደን ሽፋን 17 ነጥብ 5 በመቶ ማድረስ መቻሉን የፌዴራል የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ።
የአለም አካባቢ ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ "የስርዓተ ምህዳር ማገገም ለሀገር ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ በሀዋሳ እየተከበረ ነው።
በበዓሉ ስነ-ስርዓት የፌዴራል የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ እንዳሉት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ውጤታማ የሆነ የችግኝ ተከላና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ተከናውኗል።
በዚህም የሀገሪቱ የደን ሽፋን ከነበረበት 15 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 17 ነጥብ 5 ማድረስ መቻሉን አስታውቀዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት በተለይ መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት በተከናወነ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በርካታ ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ ልማት መረሃ ግብር አምስት ቢሊዮን ችግኝ በማዘጋጀት መትከል እንደተቻለ የገለጹት ኮሚሽነሩ፤በዚህም ተራቁቶ የነበረ ስፍራ መልሶ እንዲያገግም ማድረጉን ጠቅሰዋል።
ዘንድሮም "ኢትዮጵያን እናልብስ" በሚል መርሀ ግብር 6 ቢሊዮን ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
ከሀገር ባለፈ ለጎረቤት ሀገራትም ጭምር የተዘጋጀው የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ላይ መላው ኢትዮጵያዊ በንቃት እንዲሳተፍ ፕሮፌሰር ፍቃዱ ጥሪ አቅርበዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው፤ በክልሉ ለግንባታና ማገዶ እንዲሁም የእርሻ መሬት ለማስፋፋትና መኖሪያ ቤት ለመስራት በሚል በተፈጥሮ ሀብት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።
ጉዳቱ መልሶ እንዲያገግም ለማስቻል በየዓመቱ ችግኝ እየተተከለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ዘንድሮ በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ለሚከናወን ተከላ 300 ሚሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
አንዳንድ የውጭ ሀገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የህዳሴ ግድቡ የውሀ ሙሌት ለማስተጓጎል የሚደረጉት ጥረት የክልሉ ህዝብና መንግስት እንደሚያወግዝም አቶ ደስታ ገልጸዋል።
በሀዋሳ ከተማ በውይይት እየተከበረ ባለው የአለም አካባቢ ቀን ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው፤በሲዳማ ክልል በባህላዊ መንገድ የሚጠበቀው የወንሾ ጥብቅ ደን ጉብኝትና የችግኝ ተከላ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
በበዓሉ አከባበር ስነ-ስርዓት ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ አካላት በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ሪፖርተራችን ከሀዋሳ ዘግቧል።