ቀጥታ፡

ምርጫውን የሚታዘቡ የአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢዎች አዲስ አበባ ገቡ

አዲስ አበባ ግንቦት 28 / 2013 (ኢዜአ) ስድስተኛውን አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ የሚታዘቡ የአፍሪካ ሕብረት የረጅም ጊዜ የምርጫ ታዛቢዎች አዲስ አበባ ገቡ።

የሕብረቱ የአጭር ጊዜ ታዛቢዎች ከምርጫው አንድ ሳምንት በፊት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት ያቀረበውን ግብዣ ተከትሎ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ምርጫውን የሚታዘቡ የአፍሪካ ሕብረት የአጭርና የረጅም ጊዜ ታዛቢዎችን ስምሪት ማድነቃቸው ይታወሳል።

ሕብረቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ከሕብረቱ አባል አገራት የተውጣጡ ስምንት አባላት ያሉት የረጅም ጊዜ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን ግንቦት 25 እና 26 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ መግባቱን ገልጿል።

ታዛቢዎቹ በአጠቃላይ ምርጫ ሂደቱ ያለው የፖለቲካ ከባቢ አየር፣ የምርጫው ሕጋዊ ማዕቀፎች፣ የምርጫ ዝግጅትና አስተዳደር ግልጽነትና ውጤታማነት፣ የምርጫ ቅስቅሳ ሁኔታ የመታዘብ ስራ እንደሚያከናውኑም ተጠቅሷል።

በተጨማሪ የመገናኛ ብዙሃን የምርጫ አዘጋገብ ነጻነትና የምርጫው ተዋናዮች መብቶች አጠባበቅን የመታዘብና የመተንተን ስራ እንደሚያከናውኑም በመግለጫው ተመላክቷል።

ቡድኑ የሚሰራው ትንታኔ የአፍሪካ ሕብረት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ለሚያካሄደው ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ግምገማ ቁልፍ አካል እንደሆነም ነው የተገለጸው።

የረጅም ጊዜ የምርጫ ታዛቢዎቹ በቡድን በመከፋፈል ወደተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እንደሚሰማሩም ተጠቁሟል።

አጠቃላይ ምርጫው ከመካሄዱ አንድ ሳምንት በፊት የሕብረቱ የአጭር ጊዜ የምርጫ ታዛቢ ቡድን እንደሚቀላቀላቸውም ነው የተነገረው።

ታዛቢ ልዑኩ ሕብረቱ ምርጫን የመታዘብ፣ የምርጫ አስተዳደርና የምርጫን ዴሞክራሲያዊነት አስመልክቶ ባወጣቸው የሕግ ማዕቀፎች እንዲሁም ዴሞክራሲዊ ምርጫን መካሄዱን የሚያሳዩ ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ መለኪያዎችን አማካኝነት ምርጫውን የመታዘብ፣ መረጃ የመሰብሰብና የመተንተን እንዲሁም የመንቀሳቀስ ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለበት የአፍሪካ ሕብረት አስታውቋል።

የምርጫ ልዑኩ የስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ግኝቶችን አስመልክቶ ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ከመግለጫው በተጨማሪ አጠቃላይ ምርጫውን አስመልክቶ የመጨረሻ ዝርዝር ሪፖርት እንደሚያወጣም እንዲሁ።

ሪፖርቱ በቀጣይ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ምርጫዎች ላይ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች ላይ ምክረ ሀሳቦችን እንደሚያካትትም በመግለጫው ተመላክቷል።

የአሜሪካና የብሪታንያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች፣ የሩሲያ ሲቪል ማህበረሰብ፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ብርጌድ ቡድን፣ መቀመጫቸውን አሜሪካ ያደረጉ 'ናሽናል ዴሞክራሲ' እና 'ኢሎክቶራል ኢንስቲትዩት ፎር ሰስቴኔብል ዴሞክራሲ ኢን አፍሪካ' የተባሉ ተቋማት ስድስተኛውን አጠቃላይ ምርጫ እንደሚታዘቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ማሳወቁ ይታወሳል።

የአውሮፓ ሕብረት ምርጫውን እንደማይታዘብ ሲገልጽ ቢቆይም ምርጫውን የሚታዘቡ ስድስት አባላት ያሉት የባለሙያዎች ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልክ መግለጹ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ለመታዘብ በጋራ ለሚሰሩት ለዓለም አቀፍ ሪፐብሊካን ኢንስቲትዮት (IRI) እና ለዓለም አቀፍ ዴሞክራቲክ ኢንስቲትዮት (NDI) የምርጫ መታዘብ እውቅናን ከሳምንት በፊት መስጠቱ የሚታወስ ነው።

ስድስተኛው አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም