ብልጽግና የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የማይሰጥ ፓርቲ ነው ---ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የማይሰጥ ፓርቲ ነው ---ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ
ባህር ዳር ፤ ግንቦት 28/2013 (ኢዜአ) ''ብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ቆሞ የማይደራደርና ከማንም ጋር የማያጎበደድ ፓርቲ ነው'' ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራር ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ ገለጹ።
ፓርቲው ለስድሰተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከፍተኛው አመራሮቹ በተገኙበት በደብርታቦር ከተማ የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሄዷል።
በፈረሰኛ ሰልፍ ታጅቦ በተካሄደው የምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት ዶክተር ፈንታ ባደረጉት ንግግር "ፓርቲው ከማንም ጋር የማይጎብጥና ኢትዮጵያ እንደቀደመው ክብሯ ሁሉ ትልቅ ሀገር ሆና መቀጠል አለባት ብሎ ያምናል " ብለዋል።
ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያን የማስቀጠል ያለ ማስቀጠል እንጂ ወንበር የመለዋወጥ ጉዳይ አይደለም ያሉት ዶክተር ፈንታ ፤ ብልጽግና የተጠናከረችና ህዝቦቿ እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑባት ሀገር ለመገንባት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ፓርቲው በመሰዋዕትነት የተገኘውን የህዝብ ለውጥ ለማስቀጠልና የኢትዮጵያ ሉአላዊ ክብር ተጠብቆ እንዲቀጥል ህዝቡ ብልጽግናን በመምረጥ እንዲተባበር ጠይቀዋል።
መጪው ምርጫ አሸባሪው የትህነግ ቡድን በለውጡ ሃይል በተደመሰሰበት ወቅት የሚካሄድ በመሆኑ በተለይም ለአማራ ህዝብ ልዩ እንደሚያደርገው የገለጹት ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሜቴ አባል አቶ መላኩ አለበል ናቸው።
''የትህነግ መደምሰስ ለኢትዮጰያ ህዝብ በተለይም ለአማራ ህዝብ እንደደም ካሳ ይቆጠራል'' ያሉት አቶ መላኩ ፤ይህ ሁሉ የሆነው የለውጥ ሃይሉ በፈጠረው ተጽዕኖ እንደሆነ ተናግረዋል።
የተገኘው ለውጥ ግቡን እንዲመታና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ህዝቡ ከለውጡ ሃይል ጎን ተሰልፎ እስከ መጨረሻው እንዲያግዝ አመልክተዋል።
ከውጭም ውስጥም ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚሰሩ ሃይሎችን ሴራ በማክሸፍ በርካታ ውጤቶች እየተመዘገቡ ያሉት የሀገሬን ክብር አሳልፌ አልሰጥም በሚል ቁርጠኛ አመራር ምክንያት እንደሆነም ገልጸዋል።
ብልጽግና የተጠናከረችና ፍትሃዊነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት ፣ለስራ እድል ፈጠራና ለሴቶች እኩልነት ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ፓርቲው ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባትና በኢኮኖሚ የዳበረ ማህበረሰብ ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ አንድነት የማይደራደረውን ብልጽግናን በመደገፍ የአማራ ህዝብ ከጎኑ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
በዘመናት መካከል በደልና መከራ ቢፈራረቅበትም የአማራ ህዝብ ኢትዮጵያዊነት የማይሸረሸርና ጠንካራ ሀገር ወዳድ ህዝብ ነው ብለዋል።
ጠንካራ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ህዝቡ ብልጽግናን እንዲመርጥ መልዕክት አስተላልፈዋል።
''ብልጽግናን መምረጥ የተጠናከረችና ህዝቦቿ እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑባትን ኢትዮጵያ መምረጥ ነው'' ያሉት ደግሞ ፓርቲውን ወክለው በደብረ ታቦር ከተማ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመወዳደር በዕጩነት የቀረቡት ዶክተር ሂሩት ካሳው ናቸው።
ዶክተር ሂሩት ባስተላለፉት መልዕክትም " ታሪክ እንድንሰራ ድምጻችሁን ለብልጽግና ፓርቲ ስጡ" ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ አመራር አቶ ቀለመወርቅ ምህረቴ በበኩላቸው፤ ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሃዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፓርቲያቸው እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ብልጽግና በውስጥም ውጭም በሚሸረቡ ሴራዎች በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖም በርካታ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ውጤቶችን እያስመዘገበ ያለ ጠንካራ ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል።
ፓርቲው ለውጡን ለማስቀጠልና ኢትዮጵያን ለማሻገር ዘመኑ የዋጁና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ዕጩዎችን ማቅረቡን ጠቅሰው፤ ህዝቡም ድምጹን በመስጠት የኢትዮጵያን መጻኢ መልካም እድል ማስቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።
በደብረታቦር ከተማ ትናንት በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ስነ-ስርዓት በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ተሳትፈዋል።