በሕዳሴ ግድብ ድርድር የግብፅና ሱዳን ፍላጎት ኢትዮጵያ እንዳትጠቀም በተቻኮለ ውል ማሰር ነው-- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በሕዳሴ ግድብ ድርድር የግብፅና ሱዳን ፍላጎት ኢትዮጵያ እንዳትጠቀም በተቻኮለ ውል ማሰር ነው-- ምሁራን
ግንቦት 28/2013 (ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር የግብፅና ሱዳን ፍላጎት ኢትዮጵያ እንዳትጠቀም ለማድረግ በተቻኮለ ውል ማሰር መሆኑን የውሃ ሳይንስ እና የመካኒካል ምህንድስና ምሁራን ተናገሩ።
ኢዜአ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑትን ዶክተር የዝቤ ካሳ እና በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የመካኒካል ምህንድስና ተመራማሪዋን ዶክተር ምሥራቅ ግርማ አነጋግሯል።
ለአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት የውሃ ሃብት ጉልህ ሚና አለው ሕይወትም ነው ይላሉ የውሃ ሳይንስ ተመራማሪዋ ዶክተር የዝቤ ካሳ።
ኢትዮጵያ እንደ አባይ ወንዝ ምንጭነቷ ከናይል ተፋሰስ አኳያ ሳትጠቀም መቆየቷን ገልጸው፤ አሁን ላይ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ሃይል ለመጠቀም ስራ መጀመሯ የሚበረታታ ተግባር መሆኑን ያነሳሉ።
ለኢትዮጵያ መልካም ጅማሮ ግን በብቸኝነት የመጠቀም የቆየ ልምድ ያላቸው የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ወደ ክስና ማስፈራራት መግባታቸውን ይናገራሉ።
ሆኖም በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘሩ መልከ ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለማለፍ ይበልጥ መትጋትና መተባበር ያስፈልጋል ብለዋል።
በሃይል ማመንጫ ግድቦች ላይ እውቀትና ልምድ ያካበቱት በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የመካኒካል ምህንድስና ተመራመሪዋ ዶክተር ምሥራቅ ግርማ በበኩላችው ግድቡን ለማስተጓጎል የሚጥሩ አገራት የኢትዮጵያዊያንን ተስፋ ለማጨለም በማሰብ መሆኑን ይናገራሉ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዲዛይን ከሙያ አንጻር ማንንም የማይጎዳና ለሃይል ማመንጫነት አገልግሎት የሚውል መሆኑ ግልጽ እንደሆነም ያብራራሉ።
በመሆኑም ይህንን በግልፅ የሚታይ ዕውነታ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቅጡ ሊረዳው ይገባዋል ብለዋል።
ግብጽና ሱዳን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በተለያዩ የማደናገሪያ ሃሳቦች ለማዘግየት ከተቻለም እንዳይሳካ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ምሁራኑ ገልጸዋል።
በድርድሩ ሂደት ኢትዮጵያን በተቻኮለ ውል በማሰር በአባይ ውሃ ላይ ተጠቃሚ እንዳትሆን የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸውም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በግድቡ የሶስትዮሽ ድርድሩ የግብፅና ሱዳንን እኩይ ፍላጎት በማጤን ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርገውን መርህ መከተል እንዳለባትም መክረዋል።
ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ተስፋ ሰንቆ እየተከናወነ ያለው ፕሮጀክት "በእኔ ብቻ ልብላ በሚሉ ሃይሎች" እንዳይደናቀፍ በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን በሙያም ይሁን በገንዘብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጥል ይኖርባቸዋልም ነው ያሉት።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም ከ80 በመቶ መድረሱ ይታወቃል።