በሐረር ከተማ የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረር ከተማ የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ተካሄደ
ሐረር ፤ ግንቦት 28/2013(ኢዜአ) "ስለ አባይ እሮጣለው" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ዛሬ በሐረር ከተማ ተካሄደ።
የሐረሪ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያዘጋጀው ውድድሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ የሚከናወነውን ድጋፍ እንዲጠናከር ለማነሳሳት የተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።
በውድድሩ ከሐረር ከተማና ገጠር አካባቢ የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን በስነ-ስርዓቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በጎዳና ላይ በተካሄደው በዚሁ የሩጫ ውድድር በወንዶች ሳዳም አብዱለጢፍ፣ ሻሚ ኢብራሂም እና ጃፈር በከር በቅደም ተከተል ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ይዘው በመውጣት አሸናፊ ሆነዋል።
በሴቶች ደግሞ አዚዛ ሙክታር አንደኛ፣ ገነት ፍቃዱ እና ሙስተርያ ፈቱ ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመውጣት ውድድራቸውን አጠናቀዋል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሐረሪ ክልል ብልጽግና ጽህፈት ቤት የጥናትና ምርምር ዘርፍ ሃላፊ አቶ ኡስማኢል ዩስፍ ፤ የኢትዮዽያውያን አንድነት መገለጫ ለሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬታማነት ህብረተሰቡ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።
የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት እና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት
ሃላፊ አቶ ሄኖክ ሙሉነህ በበኩላቸው፤ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬታማ ለማድረግ የክልሉ ማህበረሰብ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ በክልሉ ከ56 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።
ዘንድሮም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ለሶስት ወራት በተዘዋወረበት ወቅት ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ መፈጸሙንም ጠቁመዋል።
የሩጫው ውድድር ዓላማ ህብረተሰቡ ለግድቡ የሚደረገውን ድጋፍ እንዲያጠናከር ለማነሳሳት የተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት አቶ ሄኖክ ህዝቡ ለግድቡ ከፍጻሜ መድረስ ሲያደርግ የቆየውን እገዛ እንዲቀጥልም ጥሪ አቀረበዋል።
በውድድሩ አሸናፊ ለሆኑ ሰዎች የዋንጫ ሽልማት በዕለቱ ክብር እንግዳ ተበርክቶላቸዋል።