ብሔራዊ የጤና ስጋት በቅንጅት ለመከላከል ስትራቴጅካዊ የድርጊት መርሃ ግብር እየተዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ የጤና ስጋት በቅንጅት ለመከላከል ስትራቴጅካዊ የድርጊት መርሃ ግብር እየተዘጋጀ ነው
አዳማ ፤ ግንቦት 27/2013 (ኢዜአ) ብሔራዊ የጤና ስጋት በቅንጅት ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር ስትራቴጅካዊ የድርጊት መርሃ ግብር እያዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ዓመታት ሀገራዊ የጤና ስጋት ከመከላከልና ከተከሰቱም ፈጣን ምላሽ በመስጠት ላይ የተከናወኑ ስራዎችና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አስቻለው አባይነህ እንዳሉት፤ ለብሔራዊ የጤና ስጋት የተቀናጀ የዘርፈ ብዙ ሴክተሮች ትብብርና ምላሽ ያስፈልጋል።
ባለፉት ዓመታት የሀገራዊ የጤና ስጋት የድርጊት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፤በዚህም በተለይዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነው የኮሮና ቫይረስን ከመከላከል አንፃር ውጤት መታየቱን ተናገረዋል።
ኮሮናን በመከላከል የታየው ውጤት የሀገራዊ የጤና ስጋት መከላከልና በሽታዎች ከተከሰቱም ፈጥኖ ለመቆጣጠር የላቀ ሚና እንደነበረው አመልክተዋል።
አሁን የቀጣይ አምስት ዓመት ብሔራዊ የጤና ስጋት መከላከልና መቆጣጠሪያ ስትራቴጅካዊ የድርጊት መርሃ ግብር እየተዘጋጀ መሆኑን ዶክተር አስቻለው ገልጸዋል።
መረሃ ግብሩን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስፈፀም የሚያስችል ሀገራዊ የጤና ስጋት መከላከልና መቆጣጠር ምክር ቤት ለማቋቋም አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በተለይ 60 በመቶ የሚሆኑት ተላላፊ በሽታዎች ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በመሆኑ ከግብርናና ጤና ሚኒስቴር፣ ዱር እንስሳትና ልማት ጥበቃ ባለስልጣን እንዲሁም ከደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ጋር የጋራ እቅድ አዘጋጅተን እየሰራን ነው ብለዋል።
የግብርና ሚኒስቴር ተወካይ ዶክተር ዮሐንስ ግርማ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ የጤና ስጋት ከሚያስከትሉ ስጋቶች መካከል ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በሽታዎችን የመለየትና የሚገኙበትን የሀገሪቱ አካባቢዎች የእንስሳት ክትባት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ከትባቱ እየተሰጠ ያለው በተለይ ድንበር ተሻገሪ የሆኑ የእንስሳት በሽታዎች፣ አባ ሰንጋና የእብድ ውሻ በሽታን ለመከላከል መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአየር ንብረት ለውጥና ብክለት ሊመጡ የሚችሉትን ጭምር ለመከላከል በአካባቢ ጥበቃ ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ዶክተር ዮሐንስ አስረድተዋል።
በተመሳሳይ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም በኮሮና በሽታ መከላከል ላይ የታየው ቅንጅታዊ ርብርብና ትብብር አሁን ሀገራዊ የጤና ስጋትን ለመከላከል ለድርጊት መረሃ ግብሩ ውጤታማነት ሁሉም መረባረብ አለበት ብለዋል።
የምክክር መድረኩ የተዘጋጀው የድርጊት መርሃ ግብሩን በሁለት ምዕራፍ በመክፈል ለቀጣይ ሶስት ዓመታት የሚከናወኑ ስራዎችን በግብዓት በማዳበር በክልሎች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ጭምር በልዩ ትኩረት እንዲተገበሩ ለማስቻል መሆኑ ተመልክቷል።
ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉበት ያለው መድረክ ለሶስት ቀናት እንደሚቆይ ኢዜአ ከአዳማ ዘግቧል።