የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃንን ተፈላጊነት ለመጨመር እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃንን ተፈላጊነት ለመጨመር እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27/2013 ( ኢዜአ) የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሩቃን በአገር ውስጥና በውጭ ተፈላጊነታቸው እንዲጨምር የትምህርት ጥራት ችግርን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ገለጹ፡፡
የትምህርት ጥራት ችግርን ለመፍታት የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ምክር ቤት ተመስርቷል።
የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ምክር ቤት ምስረታ ላይ የተገኙት ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ የትምህርት አግባብነትና የጥራት ችግርን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ከተቋማቱ የሚመረቁ ተማሪዎች በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊነታቸው እንዲጨምር ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ጥራት ችግሮችን ለመፍታት የሙያ ማህበራትን ያሳተፈ የትምህርት ጥራት ምክር ቤት መቋቋሙንም ገልጸዋል፡፡
በምክር ቤቱም የሙያ ማህበራት የትምህርት ጥራትን በየጊዜው እንዲፈትሹ፣ ጥናት እንዲያካሄዱና ስታንዳርድ እንዲያወጡ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የትምህርት ጥራት ችግርን ለመፍታት ትላልቅ ሥራዎችን ይሰራል ተብሎ ምክር ቤቱ መቋቋሙንም ዶክተር ሳሙኤል አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሙያ ማህበራት ፕሬዚዳንት ዶክተር ቢቂላ ወርቅነህ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የሚገኙ የሙያ ማህበራት የትምህርት ጥራት ምክር ቤቱ ማቋቋማቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ራሳቸውን እንዲገመግሙ፣ ፕሮግራሞቻቸውን እንዲቃኙና ችግሮች እንዲፈቱ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ስብሳቢ ወይዘሮ እምዬ ቢተው፤ ምክር ቤቱ ገለልተኛ ሆኖ የትምህርት ጥራት ችግሮችን እንዲፈታ ድጋፍ እንደሚደረግለት አረጋግጠዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጂማ ዲልቦ፤ ምስረታውን ላካሄደው የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ምክር ቤት የዕውቅና ሰርተፍኬት ሰጥተዋል።