ቀጥታ፡

በመተከል ዞን የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ይበልጥ ለማጠናከር ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በቅንጅት እንሰራለን- የዞኑ ነዋሪዎች

ግንቦት 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) በመተከል ዞን የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ይበልጥ ለማጠናከር ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዞኑ ነዋሪዎች ገለጹ።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር ዜጎችን ህይወት ከመንጥቅ ባለፈ በርካቶችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል።ከዚህ ባሻገርም በዞኑ ባለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና ፈጥሯል።

በዞኑ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ከ4 ወራት በፊት የተቋቋመው ግብረ ኃይል ከዞኑ ነዋሪዎች ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን፤ አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በዞኑ በመገኘት ቅኝት ባደረገባቸው አካባቢዎች አንጻረዊ ሰላም መስፈኑን ተመልክቷል።

አካባቢው ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ እየተመለሰ ሲሆን፤ ኢዜአ በፓዌ ከተማ በመገኘት ነዋሪዎቹን አነጋግሯል።የከተማዋ ነዋሪ አቶ አበራ ሀሰን፤ አሁን ላይ ነዋሪዎች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።

በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ገልጸው፤ እንደ ባንክና ገበያ ስፍራዎች ያሉ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ወደ ስራ መመለሳቸውን ጠቁመዋል። ዘላቂ ሰላም የሚሰፍነው ህብረተሰቡ መንግስትን ሲያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻር የተለየ ዓላማ አንግበው ሠላም ለማደፍረስ የሚጥሩ አካላትን ለጸጥታ መዋቅሩ ጥቆማ በመስጠት ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን ነው ያሉት።ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ቶሎማን አቸንፍ፤ ነዋሪዎቹ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር ተቀናጅተው መስራት ከቻሉ በዞኑ የሰፈነውን አንጻራዊ ሰላም አስተማማኝ ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች በዚህ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆኑንም ገልጸዋል።በፓዊ ከተማ በአንድ ሆቴል በስራ ላይ ያገኘነው ወጣት ካሳሁን መብሬ በዞኑ ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር በስራቸው ላይ ጫና መፍጠሩን አስታውሷል።አሁን ላይ የተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም በሆቴል ስራቸው ላይ አወንታዊ ሚና መጫወቱንም ነው የተናገረው።

የጽህፈት መሳሪያ መደብር ባለቤት የሆኑት ወይዘሮ እጹብ በለጠ፤ በዞኑ አንጻራዊ ሰላምን በማስፈን ረገድ የጸጥታ አካላት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና በማቅረብ በቀጣይ ለስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም