ቀጥታ፡

መሰረተ ልማቶችን ለህብረተሰቡ ለማዳረስ መንግስት በትኩረት እየሰራ ነው- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

ጎባ፤ ግንቦት 27/2013(ኢዜአ) የለውጡ መንግስት የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትና ሌሎችንም የመሰረተ ልማቶችን ለህብረተሰቡ ለማዳረስ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
በምስራቅ ባሌ ዞን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት "የብርሀን ለሁሉም "ፕሮጀክት የተገነቡ ሁለት በፀሐይ የኤሌክትሪክ  ሀይል  የሚያመነጩ ማዕከላት ዛሬ ተመርቀዋል።

በዞኑ ለገሂዳ ወረዳ ቤልቱና ባህማ ከተሞች የተገነቡት እነዚህ የሀይል ማመንጫ ማዕከላት የመረቁት  አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባደረጉት ንግግር የለውጥ መንግስት መሰረተ ልማቶችን በተለይም  የኤሌክትሪክ መብራት ሀይል ለህብረተሰቡ ለማዳረስ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህ ከፀሐይ የኤሌክትሪክ ሀይል የማመንጨት ልምድ በምስራቅ ባሌ ለማስፋፋት ይሰራልም ብለዋል።

በሚቀጥለው ዓመት ከፌደራል መንግስት ጋር በመተባበር በስምንት ቦታዎች ከፀሐይ የኤሌክትሪክ ሀይል ለማመንጨት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የተናገሩት አቶ ሽመልስ መንግስት የህዝቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ በመመለስ ሀገሪቱን  ወደ ብልፅግና ለማሻገር  እንደሚተጋ ተናግረዋል።

የብልፅግው ጉዞ እንዲሳካ ማህበረሰቡ በኢኮኖሚና ቴክኖሎጂ ተጠናክሮ የተገኘውን ድል በመንከባከብ ለፍሬ እንዲበቃ መረባረብ እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።

በምርቃው ስነ-ስርዓት የተገኙት የውሀ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው፤ የአካባቢው ህብረተሰብ የኤሌክትሪክ ሀይል በማግኘታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

የኤሌክትሪክ አገልግሎት በዚህ አካባቢ መገኘቱ የህክምና ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡና ትምህርት ቤቶች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲሰጡ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል ።

በፀሀይ ሀይል የሚሰሩ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማዕከላት ሀገሪቱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሀ ሙሌት ለማከናወን ዝግጅት እያደረገች ባለችበት ሁኔታ ለአገልግሎት መብቃታቸው  ልዩ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን  የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋን ለማሳደግ ሁለተኛውን የብሄራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም መጀመሩን ጠቅሰው ይህም የግል ዘርፉን በስፋት  እንደሚያሳትፍ ገልጸዋል።

መንግስት የኤሌከትሪክ ሀይል ለማዳረስ እያደረገ ባለው ጥረት አሁን ላይ  48 በመቶ የሚገኘው ሀገራዊ ሽፋን  ሙሉ በሙሉ ለማዳረስ   እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሀላፊ  አቶ ሽፈራው ተሊላ እንዳሉት፤  የምስራቅ ባሌ ዞን ፕሮጀክት  ሀገሪቱ ለጀመረችው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ተግባራዊነት በፀሀይ ሀይል የሚሰሩ 12 የፀሐይ ሀይል የኤሌክትሪክ ማዕከላት ግንባታ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

950 ኪሎዋት የኤሌክትሪክ  ሃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው የሁለቱ ማዕከላት  ግንባታ የተካሄደው "ኖሪንኮ ኢንተርናሽናል" በተባለ የቻይና ስራ ተቋራጭ መሆኑን ጠቅሰው የሰራውም  ከዓለም ባንክ በተገኘ ከ7 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መሆኑን አስታውቀዋል።

በፀሀይ ሀይል የሚሰሩት የኤሌክትሪክ ማመንጫ ማዕከላቱ የተገነቡት በተለይ ከሀገሪቱ የሀይል በቋት በርቀት ላይ በሚገኙ ማህበረሰብ አካባቢዎች ነው ብለዋል።


ከ20ሺህ ለሚበልጡ ሰዎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ እንደሚያደርጉ  ተገልጿል።


የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2025 ሁሉም ዜጎች የአገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም