የአሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ፈቃድ ቁጥጥር ባለስልጣን ባለፉት አስር ወራት ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ

ግንቦት 27/2013(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ፈቃድ ቁጥጥር ባለስልጣን ባለፉት አስር ወራት ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አደም ኑሪ  የተቋሙን የአስር ወራት እቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግጫቸውም ከመንጃ ፈቃድ እድሳት፣ የአዲስ አሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ፣ ቦሎና ሌሎች ተቋሙ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

ለ268 ሺህ ተገልጋዮች የመንጃ ፈቃድ እድሳት አገልግሎት እንዲሁም ከ208 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አሽከርካሪዎች የንድፈ ሃሳብና የተግባር ፈተና ያካተተ የብቃት ምዘና ማረጋገጫ መሰጠቱንም ተናግረዋል።

ባለፉት አስር ወራት በአጠቃላይ ከ646 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተገልጋዮች አዲስ የተሸከርካሪ ምዝገባ፣ ዓመታዊ የተሸከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ቦሎ፣ ተሸከርካሪ ስም ዝውውርና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶች መሰጠታቸውንም ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም የእጩ አሽከርካሪዎችን የተግባር ፈተና ውጤት ለማወቅ ቀናትን ይወስድ የነበረውን አሰራር በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ በ30 ደቂቃ ማከናወን መቻሉንም ዋና ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ተፈታኞች ውጤታቸው በእጅ ስልካቸው አማካኝነት በጽሁፍ እንዲደርሳቸው የሚያደርግ አሰራር መዘርጋቱንም ጨምረው ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ፈቃድ ቁጥጥር ባለስልጣን የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በ2008 ዓ.ም በአዲስ መልክ ተዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም