በዘንድሮው ምርጫ የሚፎካከሩ አራት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በማህበራዊ ፍትህና ኢንዱስትሪ ግንኙነት ፖሊሲ አማራጮች ላይ ተከራከሩ - ኢዜአ አማርኛ
በዘንድሮው ምርጫ የሚፎካከሩ አራት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በማህበራዊ ፍትህና ኢንዱስትሪ ግንኙነት ፖሊሲ አማራጮች ላይ ተከራከሩ
ግንቦት 27/2013(ኢዜአ) በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የሚፎካከሩ አራት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በማህበራዊ ፍትህና ኢንዱስትሪ ግንኙነት ፖሊሲ አማራጮች ላይ ተከራከሩ።
በክርክሩ ብልጽግና ፣ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ እና የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን (አሰማኮ) እና የኢትዮጵያ ሰራተኞች መብቶች ተሟጋች በጋራ ባዘጋጁት የክርክር መድረክ ላይ ፓርቲዎቹ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።
የብልጽግና ፓርቲን ወክለው የተከራከሩት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ፓርቲያቸው በአሰሪና ሰራተኛው መካከል የሁለትዮሽ ምክክር በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የጀመረው ሥራ ቀጣይነት እንዲኖረው ይሰራል ብለዋል።
የአሰሪና ሰራተኛ ህጉን ከማሻሻል ጀምሮ ለሰራተኞች ምቹ የስራ ከባቢ መፍጠር የደመወዝ ጣሪያ ለመወሰን የተዘጋጀውን ረቂቅ ሰነድ አጠናቅቆ ሥራ ላይ እንደሚያውል የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል።
"ብልጽግና ሰው ተኮር ነው" ያሉት ዶክተር ኤርጎጌ፣ የሰው ሀብትን በማልማት በአሰሪና ሰራተኛው መካከል ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ተመጣጣኝ እድገት ለማምጣት እንደሚሰራም ገልጸዋል።
ምርጫውን ማሸነፍ ከቻልን፤ ከለውጡ በኋላ በተሻሻለው የአሰሪና ሰራተኛ ህጉ መሰረት ሰራተኞች የጀመሩት በነፃነት የመደራጀት መብት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ የሱፍ ኢብራሂም የዜጎች ማህበራዊ ፍትህ እንዲረጋገጥና ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነት እንዲፈጠር የፖለቲካ ቁርጠኝነት ከማስፈንም ባለፈ የመዋቅርና የሥርዓት ክለሳ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ለ30 ዓመታት የቆየው ፖለቲካ የማህበራዊ ፍትህ እጦት እንደነበረበት ገልጸው፤ ችግሩ የህገ መንግሥትና የመዋቅር ነው ብሎ ፓርቲያቸው እንደሚያምን አስረድተዋል።
በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የፌደራሉን ጨምሮ የክልል ህገ መንግሥታት ማሻሻል ብሎም የመንግሥትን መዋቅርና አደረጃጀት እንዲስተካከል እናደርጋለን ብለዋል።
በህገ መንግስቱ መግቢያ ላይ የቀረበው የሀሰት ትርክት በህዝቦች መካከል ልዩነት በመፍጠር ማህበራዊ ፍትህ እንዲናጋ ማድረጉንም በአብነት ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ፓርቲ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ ፓርቲው የተቋቋመበት መርህና በኢትዮጵያ እውን እንዲሆን የሚፈልገው የዜጎችን ማህበራዊ ፍትህ ማረጋገጥ ነው ብለዋል።
የማህበራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ ጠንካራ የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራም የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ማረጋገጥ ዴሞክራሲን ማስፈን ይገባል ብለዋል።
ዜጎች ከማህበረሰቡ ጋር ባላቸው ተሳትፎ ተመጣጣኝ እድል የጎላ ሚናና ክብር እንዲሁም በምርትና አገልግሎቶች የሚኖራቸውን ድርሻ ፍትሃዊ ለማድረግ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በአሰሪና ሰራተኞች መካከል መልካም መስተጋብር እንዲኖር ሰላማዊ የኢንዲስትሪ ግንኙነት በመፍጠር የሰራተኖችን የደመወዝ መጠን ምርታማነት በጨመረ ቁጥር ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለአብነት የድርጅቱ የምርት እድገት አምስት በመቶ ቢያስመዘግብ፤ የሰራተኞች ደመወዝ ቢያንስ ሁለት በመቶና ከዚያ በላይ ማደግ ይገባዋል ብለዋል።
ማህበራዊ ፍትህ የሚረጋገጠው ደመወዝ በመጨመር ብቻ አይደለም የሚሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ደረጃውን የጠበቀ የትምህርትና የጤና አገልግሎት ብሎም የጡረታን ገቢ ለማሳደግ ኢዜአ ይሰራል ብለዋል።
የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ተወካይ አቶ ሰኢድ ጌታሁን ፓርቲያቸው በምርጫው ቢያሸንፍ ሰራተኞችን በስራቸው ደስተኛ ሆነው እንዲቆዩ የሚያደርግ ከባቢ በመፍጠርና የአሰሪዎችን ምርታማነት በማሳደግ ሁለቱም አሸናፊ የሚሆኑበት ሥርዓት እንደሚዘረጋ ገልጸዋል።
የማህበራዊ ፍትህ መርሆዎች የሆኑት እኩል የሀብት/አገልግሎት ክፍፍል፤ ተመጣጣኝ የሥልጣን ድልድል፤ አካታችነት፤ አሳታፊነትና የሰብዓዊና ዲዴክራሲያዊ መብቶች እውን እንዲሆኑ እናደርጋለን ብለዋል።