ቀጥታ፡

ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የሰባዊ ድጋፍ ቁሳቁስ ወደ መቀሌ፣ መተከልና አጣዬ እየተጓጓዘ ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የሰባዊ ድጋፍ ቁሳቁስ ወደ መቀሌ፣ መተከልና አጣዬ በመጓጓዝ ላይ መሆኑን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። 

ሰባዊ ድጋፉ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ በባህልና ቱሪዝም እንዲሁም በጤና ሚኒስቴር በኩል የተሰበሰበ መሆኑም ተገልጿል።

የድጋፉን አጠቃላይ ሂደት አስመልክቶ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ድጋፉ በትግራይ ክልል እንዲሁም በመተከልና በአጣዬ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል ነው ብለዋል።

ድጋፉ አልባሳት፣ የንጽህና መጠበቂያና የቤት ቁሳቁሶችን ያካተተ ሲሆን፤ ከተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት መሰብሰቡም ተገልጿል።

ግምቱ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ሲሆን 66 ሺህ ኪሎ ግራም ለመቀሌ፣ 36 ሺህ ኪሎ ግራም ለመተከል፣ እንዲሁም 35 ሺህ  ኪሎ ግራም ለአጣዬ የተመደበ መሆኑን ገልጸዋል።

በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ወደ ትግራይ ክልል መቀሌ የሚሄደው ድጋፍ የሚያስተባብሩ ይሆናል።

ወደ መተከል የሚላከውን ድጋፍ የጤና ሚኒስሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ፤ ወደ አጣዬ የሚላከውን ደግሞ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስተሯ ዶከተር ሂሩት እንደሚያስተባብሩት ተገልጿል።

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር ወደ ትግራይ ክልልና ወደ መተከል የሚሄደው ድጋፍ ከዛሬ ጀምሮ እየተጓጓዘ መሆኑንም ዶክተር ኤርጎጌ ተናግረዋል።

ከነገ ግንቦት 28/9/2013 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ወደ አጣዬ ድጋፉ የሚጓጓዝ ይሆናል።

በአምስት ቀናት ውስጥ በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች ለማድረስ እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሯ ጨምሮ ገልጸዋል።

በቀጣይም በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በጤና ሚኒስቴር እንዲሁም በሰላም ሚኒስቴር በኩል የተዋቀረው ግብረ ኃይል የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም