በምስራቅ ባሌ ዞን በፀሐይ ሀይል የሚሰሩ ሁለት የኤሌክትሪክ ሀይል ማዕከላት ተመረቁ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ባሌ ዞን በፀሐይ ሀይል የሚሰሩ ሁለት የኤሌክትሪክ ሀይል ማዕከላት ተመረቁ
ጎባ፤ ግንቦት 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) በምስራቅ ባሌ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት “የብርሀን ለሁሉም” ፕሮጀክት የተገነቡ ሁለት የፀሐይ ሀይል ማዕከላት ዛሬ ተመርቀዋል።
ማዕከላቱ የተገነቡት በዞኑ ለገሂዳ ወረዳ ቤልቱና ባህማ ከተሞች ነው።
950 ኪሎዋት የኤሌክትሪከ ሃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው የማዕከላቱ ግንባታ የተካሄደው "ኖሪንኮ ኢንተርናሽናል" በተባለ የቻይና ስራ ተቋራጭ ነው።
ለማዕከላቱ ግንባታ ከዓለም ባንክ በተገኘ ከ7 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መሆኑን በምረቃው ስነ-ስርዓት ወቅት ተገልጿል።
ይህም ኢትዮጵያ ለጀመረችው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ተግባራዊነት በፀሀይ ሀይል የሚሰሩ 12 የፀሐይ ሀይል የኤሌክትሪክ ማዕከላት አካል እንደሆነ ተመልክቷል።
በፀሀይ ሀይል የሚሰሩት የኤሌክትሪክ ማመንጫ ማዕከላቱ የተገነቡት በተለይ ከሀገሪቱ የሀይል ቋት በርቀት ላይ በሚገኙ ማህበረሰብ አካባቢዎች ነው።
የኤሌክትሪክ ማመንጫ ማዕከላቱ ከ20ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ እንደሚያደርጉም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2025 ሁሉም ዜጎች የአገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑም ተመልክቷል።