ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተመሰረተ

ሐረር፤ ግንቦት 27/ 2013(ኢዜአ) በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሐረሪ ክልል የሚወዳደሩ ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መሰረቱ።

ትናንት ጀምሮ በሐረር ከተማ ባካሄዱት የስብሰባ መድረክ  የጋራ ምክር ቤቱን የመሰረቱት ብልፅግና ፓርቲ፣ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ ፣ የሐረሪ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት እና እናት ፓርቲ ናቸው፡፡


በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሐረሪ ክልል ማስተባባሪያ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ምርጫ ኦፕሬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ቦጋለ እንደገለጹት፤ ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ህጋዊ እውቅና አግኝተው የሚንቀሳቀሱ ሰባት  የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መመስረታቸውን አረጋግጠዋል።

የጋራ ምክር ቤት መመስረት የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሂደት የሚያጋጥማቸውን  ችግሮችን እርስ በእርስ በመመካከር ለመፍታት ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡


ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የላቀ የሚኖረው ከመሆኑም በላይ በቅድመና ድህረ ምርጫ ወቅት የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡


የብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል የፖለቲካና ሲቪክ ማህበራት ዘርፍ ሃላፊው አቶ ሐሰን አብዲ በበኩላቸው፤ የጋራ ምክር ቤት መኖሩ ምርጫው ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ዲሞክራሲያዊ እና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡


ፓርቲዎች የምርጫ ህግና የስነምግባር ደንብ ባከበር መልኩ እንዲቀሳቀሱ ከማድረግ አንፃርም ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡


በምርጫ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችንም በምክክር መፍታት ያስችላል ያሉት አቶ ሐሰን፤ ይህም የሀገሪቱን ዴሞክራሲ እንዲጎለብት እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡


ብልጽግና በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲዳብር በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ነው፤ ምርጫው የተሳካ እንዲሆን በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡


የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ የሐረሪ ክልል ሊቀመንበር አቶ መሀመድ ሀሰን አደም በበኩላቸው ፤የምክር ቤቱ መመስረት ምርጫውን ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ እና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ችግሮች ከመፈጠራቸው ቀድሞ በመረዳት ለመስራት እንደሚያግዝና ፓርቲያቸውም ምክር ቤቱ እንዲቋቋም የበኩሉን ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ አውስተዋል። 

ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ምርጫውን ሰላማዊ እንዲሆን እያደረገው ያለው ጥረቱን ያጠናክራል ብለዋል፡፡


የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ን በመወከል በሐረሪ ክልል በዕጩነት የሚወዳደሩት አቶ አዝማች ጌጡ እንደተናገሩት፤ የምክር ቤቱ መመስረት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚገጥማቸውን ችግሮች በጋራ ለመፍታተ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።


ኢዜማ ሐረር ቅርንጫፍም ህግና መመሪያ አክብሮ በመንቀሳቀስ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል ብለዋል።


የጋራ ምክር ቤቱን የመሰረቱት የፖለቲካ ፖርቲዎች የተለያዩ ኮሚቴ አባላትን በመምረጥ ሰብሰባቸውን ዛሬ አጠናቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም