ቀጥታ፡

አሁን የገጠመንን አገራዊ ችግር ለመፍታት መናበብና ማመዛዘን ያስፈልጋል- ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ

አዲስ አበባ ፣ግንቦት 27/2013/ኢዜአ/ ''አሁን የገጠመንን አገራዊ ችግር ለመፍታት መናበብና ማመዛዘን ያስፈልጋል'' ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያ ልማት ማህበር (ኦልማ) በአዲስ አበባ ደረጃ ዓመታዊ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት መልእክት አስተላልፈዋል።

በመልእክታቸው''አንድነታችሁን ጠብቁ አገራችሁን አሻግሩ'' ያሉ ሲሆን ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ፈተና ለማለፍ ማመዛዘንና መናበብ ያስፈልጋል ብለዋል።

"ለበርካታ አመታት እየተጣላን ቆይተናል" ከዚህ በኋላ ግን ምኞታችን ብልጽግና በመሆኑ ለዚህ መትጋት አለብን ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ማሸነፍን እናውቅበታለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ያገኘነውን ድል አጥብቀን መያዝና ወደ ብልጽግና መሻገር አለብን ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ ሁሉም ዜጋ ሊተጋ ይገባል ብለዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንውሚ አዴሲ በበኩላቸው ባንኩ የረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ አጋር በመሆን በአገሪቷ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗ ለምታከናውናቸው የልማት ስራዎች ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት።

"አንድነት ለልማት" በሚል መሪ ሀሳብ የኦሮሚያ ልማት ማህበር (ኦልማ) በአንድነት ፓርክ ዓመታዊ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ማጠቃለያውን አድርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም