ቀጥታ፡

ውስጣዊ አንድነታችንን በማጠናከር ውጫዊ ጣልቃ ገብንትን በጋራ መመከት አለብን- የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

አዲስ አበባ ግንቦት 27/2013 /ኢዜአ/ ኢትዮጵያዊያን ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር ውጫዊ ጣልቃገብነትን በጋራ መመከት አለብን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።

ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይዋን በውጭ ጣልቃ ገብነት ሳይሆን በራሷ አቅም መፍታት ትችላለችም ብለዋል።

የሕብር ኢትዮጵያ ሊቀ መንበር አቶ ግርማ በቀለ፣ የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ሰለሞን ታፈሰና የወላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀ መንበር አቶ ተክሌ ቦረና ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ፖለቲከኞቹ በታላቁ የኢተዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ በግብፅና በሱዳን በኩል እንዲሁም በቅርቡም በአሜሪካ በኩል የወጣው የባለስልጣናት የጉዞ እግዳ ተገቢነት የሌለው ነው ብለዋል።

ይህን ውጫዊ ጣልቃገብነት ኢትዮጵያዊያን ውስጣዊ አንድነታችንን በማጠናከር በጋራ መመከት አለብን ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የሕብር ኢትዮጵያ ሊቀ መንበር አቶ ግርማ በቀለ መንግስት በዲፕሎማሲው፣ በሰላምና ሰብዓዊ መብቶች ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈ አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና የሉዓላዊት ጉዳይ መሆኑን ለሁላችንም የማያሻማ ጉዳይ ነው ብለዋል።

"እኛ ኢትዮያውያን የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ለአገር ሉዓላዊነት በጋራ እንቆማለን፤ በአባይ ጉዳይም ልዩነት የለንም" ብለዋል።

"ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር ነች፣ ማንም ሊያንበረክካት አይችልም" ያሉት ደግሞ የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ሰለሞን ታፈሰ ናቸው።

ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን በረሷ መፍታት እንጂ የማንም ጣልቃ ገብነት እንደማያስፈልጋትም ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ መደረግ እንዳለበት ጠቅሰው፤ በአገር ጉዳይ ላይ በጋራ ቆመን የሚገጥሙንን ችግሮች ሁሉ በጋራ መፍታት ይገባናል ብለዋል።

የወላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀ መንበር አቶ ተክሌ ቦረና በበኩላቸው ግብጽና ሱዳን የኢትዮጵያን ውስጥዊ አቅም በማየት የተዳከመች ከመሰለቻው ትንኮሳ ማድረጋቸው የተለመደ አካሄድ መሆኑን አንስተዋል።

አሁንም ከአሜሪካና መሰል አገራት ድጋፍ በማግኘት የጦርነት ቅስቀሳ እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፤ በመሆኑም ውጫዊ ጣልቃ ገብነትን ለመከላከል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ውስጣዊ አንድነቱን ማጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።

ፓርቲያቸው በቅርቡ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባት ያሳለፈውን ውሳኔ እንደሚያወግዘውም ገልጸዋል።

ግብፅ በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ እ.ኤ.አ. የ1929 እና የ1959 ዓ.ም የፈረምኩት ተጠቃሚ የሚያደርገኝ የቅኝ ግዛት ውል ሊከበርልኝ ይገባል የሚለውን አቋሟን አሁንም አልቀየረችም።

በ1929 የተፈረመው የቅኝ ግዛት ስምምነት ቀጣይነት እንዲኖረው ግብፅ ስትሻ ሱዳንም በ1959 ከግብጽ ጋር የተፈራረምኩት የአባይ ውሃ አጠቃቀም ስምምነት ይቆይልኝ የሚል አቋም አላት።

በዚህ ስምምነት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ባለመካተታቸው በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1999 ሁሉን የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ያጠቃለለ ስምምነት ለመድረስ የሚረዳ አንድ እቅድ ቢቀርብም ግብጽና ሱዳን እቅዱን ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም