ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል ጉዳይ የሚነሱ ዓለም አቀፍ ክስና ወቀሳዎች እውነታን የካዱና በኢትዮጵያ ላይ ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር --የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት

ግንቦት 26/2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል ባለው ወቅታዊ ጉዳይ የሚነሱ ዓለም አቀፍ ክስና ወቀሳዎች እውነታን የካዱና በኢትዮጵያ ላይ ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር መሆኑ ተገለጸ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት የውጭ ቋንቋና ዲጂታል ሚዲያ ሃላፊ ብለኔ ሥዩምና የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶክተር ጌዴዎን ጢሞቲዎስ በጉዳዩ ላይ ለውጭ ሚዲያዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በትግራይ ክልል ጉዳይ የሚነሱ ዓለም አቀፍ ክስና ወቀሳዎች እውነታን የካዱና በኢትዮጵያ ላይ ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር መሆኑን ገልጸዋል።

የሕወሃት ቡንድ ስልጣን ላይ በነበረበት ላለፉት 30 ዐመታት የፈጸማችውን መልከ ብዙ ወንጀሎችና ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አስታውሰዋል።

ህወሃት በኢትዮጵያ በብሄር፣ ሃይማኖትና ጎሳ ከፋፍሎ ለማጋጨት የሄደበትን ርቀት፣ ብሎም ለጦርነቱ መንስኤ የሆነው የሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመውን ጥቃት ለጋዜጠኞቹ አስረድተዋል።

የህወሃት ቡድን የሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት የአገር ህልውናን ለመጠበቅ የህግ ማስከበር እርምጃ መውሰዱንም አንስተዋል።

የሕግ ማስከበር እርምጃው ከተጠናቀቀ በኋላም የመልሶ ግንባታና ሰብአዊ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።

የፌዴራል መንግስት መንግሰታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በአንደኛ ሁለተኛና ሶስተኛ ዙሮች የተጠናከረ ሰብአዊ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ከሰብዓዊ ርዳታዎች መካከልም በክልሉ ከሚገኙ 93 ወረዳዎች 5 ቢሊየን ብር የሚገመት ከ166 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብ ነክ እርዳታ መቅረቡን ገልፀዋል።

ሰብዓዊ እርዳታውን የሚያስፈጽሙ 6 ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በኩል ሰብዓዊ ደጋፉ እየደረሰ መሆኑን ገልጽው፤ ይህም መንግስት መንግስታዊ ካልሆኑ አጋር አካላት በጋራ እየሰራ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከአጋር አካላት ጋር ለመስራት ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ገልጸው፤ መንግስት በትግራይ ክልል መልሶ ማቋቋም ስራዎችን ከማገዝ ይልቅ ስራውን የሚያጠለሹና ለተጎጂው ህዝብ የማይበጁ አሉባልታዎች እንደሚናፈሱ አንስተዋል።

በትግራይ ክልል ጉዳይ የሚነሱ ዓለም አቀፍ ክስና ወቀሳዎች እውነታን የካዱና በኢትዮጵያ ላይ ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።

በክልሉ ከ97 ሺህ የአስቸኳይ ርዳታ መስጫ መጠለያዎች ምግብ ነክ እርዳታዎች እየቀረቡ መሆኑን ገልጸው፤ ምግብ ነክ ባልሆኑ ቁሳቀሱች አቅርቦት ውስንነት እንዳለ አንስተዋል።

በክልሉ ለሚገኙ የጤና ተቋማት አገልግሎት እንዲሰጡ በጤና ሚኒስትር በኩል 72 ሚሊየን ብር የሚገመቱ መድሃኒቶች፣ 12 አንቡላንሶች መቅረባቸውን፣ ከ60 በላይ ተንቀሳቃሽ የጤና አገልግሎት ሰጭ ቡድኖች መቋቋማቸውን አንስተዋል።

ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በጤናው ዘርፍ ላይ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ዙሪያ የሚነሱ ወቀሳዎቸም መሰረተ ቢስ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ 537 ሺህ 728 በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ፣ ከ73 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘርና ሌሎች ግብዓቶች በግብርና ሚኒስቴር በኩል ተደራሽ መደረጉንም አስረድተዋል።

የትምህርት ተቋማት እንዲከፈቱ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ የተለያዩ ተግበራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም