በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር እየተሰራ ነው- ግብረ ኃይሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር እየተሰራ ነው- ግብረ ኃይሉ
ግንቦት 26/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በአከባቢው የተቋቋመው ግብረ ኃይል ገለጸ።
በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን አንጾኪያ ገምዛ ወረዳና በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ዳዋ ጨፋ ወረዳና ከሚሴ ከተማ አስተዳደር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያስችል መርሃ ግብር ተከናውኗል።
በአካባቢው የተቋቋመው ግብረ ኃይል አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አቢቼ፤ ውይይቱ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ የሰላምና የአብሮነት እሴቶችን የማጠናከር አላማ እንዳለው ገልጸዋል።
ግብረ ኃይሉ በአካባቢው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን በመስራት ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት አስተባባሪው፣ በዋነኝነት ግጭቶች እንዲቆሙና ዳግም እንዳይከሰቱ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ሕዝብ ለሕዝብ በማገናኘትና በማወያየት ችግሮችን ለማቃለልና እርቀ ሰላም ለመፍጠር ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በአካባቢው በተፈጠረው አለመረጋጋት አካባቢውን የለቀቁ ዜጎች ወደ ቀያቸው የመመለስና የወደሙ ቤቶችን መልሶ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ሌተናል ጄኔራል ደስታ ተናግረዋል።
የአንጾኪያ ገምዛና የዳዋ ጨፋ ወረዳዎችና የከሚሴ ከተማ አስተዳደር አመራሮች፤ ማህበረሰቡ እርስ በእርስ የተጋመደና የተዋለደ መሆኑን ጠቅሰው፣ የግጭቱ መንስዔዎች በመመርመር መፍትሄ መስጠታቸውን አመልክተዋል።
ዞኖቹ ግጭት መንስኤን በመፍታት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነታቸውን እንዲያጠናክሩና ሰላማቸውን እንዲያስጠብቁ አሳስበዋል።
አቶ ሸሪፍ ቃሲም የዳዋ ጨፌ ወረዳ አስተዳዳሪ ለግጭት መንስዔ የሆኑ ነገሮችን ጭምር እየፈታን ጥፋት እንዳይጠፋ፣ ንብረት እንዳይወድም እና አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ እንሰራለን ብለዋል።
አቶ ደምሴ አበራ የአንጾኪያ ገምዛ ወረዳ አስተዳዳሪ ቀድሞ ችግር አንዳይፈጠር የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የወረዳ አመራሮች ችግር ሊፈጠርበት የሚችል አካባቢ ቀድሞ በመገኘት በማንኛውም በኩል ተንኳሽ እንዳይኖር ቀድሞ በመስራት በቀጠናው ችግር ሳይከሰት ቆይቷል ብለዋል።
የአብሮነት ሥርዓቱን ላዘጋጁት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ነዋሪዎች ምስጋና ቀርቦላቸዋል።