ሀገር በቀል ዕውቀት ለሀገራዊ ችግሮች መፍትሄ በመሆናቸው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል-የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር በቀል ዕውቀት ለሀገራዊ ችግሮች መፍትሄ በመሆናቸው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል-የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር
አርባ ምንጭ ግንቦት 26/2013( ኢዜአ) ሀገር በቀል ዕውቀቶች ሀገራዊ ችግሮችን ከመፍታት አንጻር ጉልህ ሚና ያላቸው በመሆኑ ለዘርፉ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
“ሀገረሰባዊ ዕውቀቶች ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
የባህልና ቱርዝም ሚኒስቴር ዴኢታ ብዙነሽ መሠረት በወቅቱ እንዳሉት ሀገራችን የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ እንደመሆንዋ የመጠነ ብዙ ባህልና ሀገር በቀል ዕውቀቶች ባለጸጋ ናት ።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በመጠቀም የሚያጋጥመውን ችግር በመፍታት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙን ሲያስጠብቅ መኖሩን ጠቁመዋል።
"ሀገራችን ከምትታወቅባቸው ሀገር በቀል ዕውቀቶች መካከል የባህል ህክምና፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ ቁጠባ፣ ባህላዊ የአስተዳደር ስርአት፣ ዘመን አቆጣጠር፣ ዕደጥበብና የእርቅ ስርአት ተጠቃሽ ናቸው" ብለዋል።
"ለሀገር ግንባታ ጎልህ ሚና ያላቸው ሀገር በቀል ዕውቀቶች ትኩረት ባለማግኘታቸው ተገቢውን ጥቅም ሳናገኝባቸው ቆይተናል" ሲሉም ተናግረዋል።
ሀገር በቀል ዕውቀቶች ሀገራዊ ችግሮችን ከመፍታት አንጻር ጉልህ ሚና ያላቸው በመሆኑ ለዘርፉ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሀገረሰባዊ ዕውቀቶችን በማጥናትና በማልማት ለሀገራዊ ሁለንተናዊ ዕድገት ለማዋል እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል ።
በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዘርፉ የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከት እንደሚገባቸው አስገንዘበዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው መንግስት የሀገራችን ብልጽግና ለማረጋገጥ እያከናወነ ያለውን ስራ ለማሳካት ሀገረሰባዊ ዕውቀቶች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
"ዩኒቨርሲቲው በሀገራችን ካሉ ስምንት የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ እንደመሆኑ መጠን የሀገር በቀል ዕውቀቶችን ሚና ለማጎልበት ጥናትና ምርምር በማድረግ የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል" ብለዋል።
ሀገር በቀል ዕውቀት የሀገራዊ ችግር በመፍታት ጉልህ ድርሻ ስላለው ከዘመናዊ ዕውቀት ጋር ተጣምረው ሊሰራባቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በአውደ ጥናቱ በሀገር በቀል ዕውቀቶች ዙሪያ የተካሄዱ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።