የኢትዮጵያ የልማት አጀንዳዎች በውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጣልቃ ገቦች አይሰናከልም-- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የልማት አጀንዳዎች በውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጣልቃ ገቦች አይሰናከልም-- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ
ጋምቤላ ፤ ግንቦት 26/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የቀየሰቻቸው ወሳኝ የልማት አጀንዳዎች በውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጣልቃ ገቦች እንደማይሰናከል የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።
የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ማጃንግ ዞን በመንጌሽ ወረዳ ተጀምሯል።
በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳዳሩ እንዳሉት፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ምዕራፍ የምትሸገርባቸውን የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት፣ ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫና ሶስተኛውን አረንጓዴ አሻራ ልማት በስኬት ለማጠናቀቅ እየሰራች ነው።
እነዚህን ወሳኝ የልማትና የፖለቲካ አጀንዳዎች ለማሰናከል የውጪ ኃይሎችና የውስጥ ባንዳዎች ጫና እየፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የኢትየጵያን ልማትና ሰላም በማይፈልጉ ኃይሎች የተጠነሰሰው ሴራና ጫና መቼውንም እንደማይሳከላቸው ገልጸዋል።
አሁን ላይ እየተካሄዱ ያሉት ወሳኝ የልማትና የፖለቲካ አጀንዳዎችም በኢትዮጵያውን የጋራ ጥረት በስኬት እንደሚጠናቀቁ ጥርጥር የለውም ብለዋል።
የክልሉ መንግስትም ለዚሁ ወሳኝ አጀንዳዎች ስኬት የድርሻውን ለመወጣት በትጋት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በክልሉ ሶስተኛውን ዙር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከለ መርሃ ግብርም መጀመሩን አስታውቀዋል።
በክልሉ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለመትክል መታቀዱን ርዕሰ መስተዳደሩ ተናግረዋል።
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡጁሉ ሉዋል በበኩላቸው፤ ዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራን ልማት ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ በስኬት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የህብረተሰቡን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በክልሉ በ68 የችግኝ ማፍያ ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ኢኮኖሚዊ ጠቀሜታ ያላቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የህዝቡ ተሳትፎ ሊጨምር እንደሚችል ተናግረዋል።
አቶ ኡጁሉ እንዳስረዱት፤ የችግኝ ተከላው በማጃንግ ዞን መንጌሽ ወረዳ ሊጀመር የቻለው ዝናቡ ቀድሞ የሚጀምረበትና ቀደም ሲል የተፋሰስ ልማት በስፋት የተካሄደበት አካባቢ በመሆኑ ተመርጦ ነው።
በስፍራው የተገኙት የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ/ ጋህነን/ ሊቀመንበር አቶ ፒተር አማን በሰጡት አስተያየት፤ የአረንጓዴ አሻራ ልማትም፣ የህዳሴ ግድብና በሌሎች ብሔራዊ ጥቅሞች ዙሪያ ፓርቲው ከመንግስትና ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
"በተለይም አሁን ላይ ከህዳሴ ግድብና ሌሎች አጀንዳዎች ጋር ተያይዞ እየተቃጣብን ያለውን የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመመከት አንድነት የምንቆምበት ጊዜ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሲጀመር ባለፉት ዓመታት በዘርፉ የተከናወኑ የዘርፉ ልማት ስራዎችም በክልሉ ከፍተኛው አመራሮች ተጎብኝቷል።