ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች የምገባ አገልግሎት የሚሰጥ ተጨማሪ ማዕከል ስራ ጀመረ

አዲስ አበባ ግንብት 26/2013/ኢዜአ/ የአዲስ አበባ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ አንድ ሺህ ዜጎች የምገባ አገልግሎት የሚሰጥ ተጨማሪ ማዕከል ስራ ጀመረ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት በልደታ ክፍለ ከተማ የተገነባው 4ኛው አዋሽ ቅርንጫፍ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማእከል በይፋ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

ምክትል ከንቲባዋ በንግግራቸው ችግሮቻችንን የምናቃልለው ስንተባበር በመሆኑ ለሰው ልጆች ቅድሚያ በመስጠት የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ማሳካት አለበን ብለዋል።

የምገባ ማዕከላቱ በበጎ አሳቢ ግለሰቦች እና ተቋማት ትብብር እውን መሆናቸውን በመጥቀስ ምስጋናቸውን አቅርበው በከተማዋ የሚስተዋሉትን ማህበራዊ ችግሮች በአብሮነት በመተባበር ማቃለል እንደሚቻል አሳይተውናል ብለዋል።

ከጎዳና ላይ የሚነሱ ወገኖች በቀጣይ ስልጠና ወስደው ወደ ስራ እንደሚሰማሩና እስከዛው ግን በምገባ ፕሮግራሙ ታቅፈው እንደሚቆዩ ተናግረዋል።

የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ስራአስፈጻሚ ወይዘሮ ሽታዬ መሃመድ የምገባ ፕሮግራሙ የኑሮ ጫናን ከማቃለል በተጨማሪ የህዝብ ወገንተኝነትን ያሳየ ነው ብለዋል።

በክፍለ ከተማው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና ድጋፍ የሚሹ ከ9 ሺህ በላይ ዜጎች መኖራቸውን ጠቁመው ከነዚህም ለአንድ ሺህ ዜጎች የምገባ እድል መመቻቸቱን ገልጸዋል።

መንግስት ለተማሪዎች የሚሰጠው የምገባ ፕሮግራም በትምህርት ጥራት ላይ በጎ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፤ ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን መመገብ የዜግነት ግዴታ መሆኑን ገልጸዋል።

እድገት ማምጣት የሚቻለው ሁሉንም ዜጋ በማሳተፍና እኩል ተጠቃሚ በማድረግ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ለሃገር ሰላምና አንድነት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰዋል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ አዋሽ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን፣ ቢጂአይ ኢትዮጵያ እና ሌሎች አጋር አካላት በተስፋ ብርሀን የምገባ ማዕከል 1 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የምገባ አገልግሎት አንደሚሰጡ በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

በመዲናዋ የተስፋ ብርሃን በሚል በተሰየሙና በአራዳ፣ በቦሌ እና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በሚገኙ አላሙዲን የምገባ ማዕከላት በቀን አንድ ጊዜ መመገብ ለማይችሉ ነዋሪዎች የምገባ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወሳል።

በዚህም ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ 10 ሺህ ዜጎችን ከጎዳና በማንሳት ወደ ቤተሰብ የመቀላቀል፣ ስራ የመፍጠርና የምገባ ፕሮግራም ሲያከናውን መቆየቱ ተገልጿል።

ከተማ አስተዳድሩ ከዚህ በተጨማሪ ከ600 ሺህ በላይ ለሚደርሱ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት እንደሚያደርግ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም