ቀጥታ፡

የአየር ብክለት ችግርን ለማቃለል የሚያስችል የአየር ጥራት አስተዳደር እቅድ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2013/ኢዜአ/ በመዲናዋ እየተባባሰ የመጣውን የአየር ብክለት ችግር ለማቃለል የሚያስችል የአየር ጥራት አስተዳደር እቅድ ማዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወዬሳ ፈይሳ፤ የኮሚሽኑን የአየር ጥራት አስተዳደር እቅድ ለባለድርሻ አካላት ይፋ አድርገዋል።

በአዲስ አበባ የአየር ብክለት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን አብራርተው ችግሩን ለማቃለል በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የአየር ጥራት አስተዳደር እቅድ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።

እቅዱ በከተማዋ የአየር ብክለት የሚያስከትሉ ምክንያቶችን በመለየትና የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ የመከላከል ተግባራት ላይ በማተኮር መዘጋጀቱንም አብራርተዋል።

የፋብሪካዎች ተረፈ ምርት እና የቆሻሻ አወጋገድ በየቦታው መሆኑ ለችግሩ መባባስ አይነተኛ ምክንያት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ የአየር ጥራት ችግር እየገጠመው በመሆኑ ዘላቂ መፍትሔ ለመሻት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

የኮሚሽኑ የአየር ንብረት ለውጥ ቡድን መሪ ፋንቱ ክፍሌ እቅዱን ባቀረቡበት ወቅት እንደገሉጸት ይፋ የሆነው እቅድ በመዲናዋ የአየር ጥራትን ከፍ ለማድረግ ዋነኛ መፍትሔው ባለድርሻዎችን ማሳተፍ መሆኑን ያስቀምጣል።

በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2001 እስከ 2025 የሚተገበረው እቅድ በመዲናዋ ከአየር ብክለት ጋር ተያይዞ እየተከሰቱ ያሉ የመተንፈሻ አካላት ችግሮችን ለመቀነስ ያስችላልም ተብሏል።

በመሆኑም ከፋብሪካዎች፣ ከትራንስፖርት ዘርፉና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ወደ አየር የሚለቀቁና የአየር ጥራትን የሚበክሉ ብናኞችን መቀነስ ላይ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በእቅዱ መሰረት የከተማዋን የአየር ብክለት ሁኔታ የሚለኩ መሳሪዎችን በተመረጡ ቦታዎች በማስቀመጥ የብክለት መጠንን ማየትና ምንጮቹን ለይቶ መፍትሔዎችን ማስቀመጥ ይሆናል።

ከፋብሪካዎች ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ በካይ ጋዞችን በሒደት በአዳዲስ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ለመቀነስ የሚቻልበትን የጋራ አሰራር ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።

በዓለም ሪሶርስ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ከተሞች ዳይሬክተር አክሊሉ ፍቅረስላሴ፤ ኢንስቲትዩቱ የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ በርካታ ጉዳዩች ላይ ጥናት አድርጎ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ብለዋል።

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተካሔዱ ጥናቶችን መነሻ በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ ለአየር ጥራት ማነስ ዋነኛ ምክንያት የሆኑት ላይ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከአየር ጥራት መጓደል ጋር በተገናኘ በአለም ላይ ከዘጠኝ ሰዎች አንዱ ለህልፈት እንደሚዳረግ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

እኤአ በ2019 የወጣ አንድ መረጃ እንደሚያመለክተው ከአፍሪካ ከተሞች በአየር ብክለት የጋናዋ ዋና ከተማ አክራ፣ የግብፅ ካይሮ፣ የናይጀሪያዋ ሌጎስ ከአንድ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ አዲስ አበባን በአራተኛ ደረጃ አስቀምጧታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም