የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የ2013 ዓ.ም አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የ2013 ዓ.ም አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ጀመሩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የሚገኙ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የ2013 ዓ.ም አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ጀመሩ።
ዩኒቨርሲቲዎቹ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በሌሎች ዘርፎችም በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸው ከተማ አቀፍ ፎረም አቋቁመዋል።
የአዲስ አበባ፣ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን፣ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ በእንጦጦ ፓርክ ችግኝ ተክለው መርሃ ግብሩን በይፋ ጀምረዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፤ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማርና ምርምር ሥራው ባሻገር በማህበረሰብ አገልግሎት በየዓመቱ ለአረንጓዴ አሻራ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።
ዩኒቨርሲቲው በ2012 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ከ4 ሺህ 500 በላይ ችግኞችን በመትከል ከ87 በመቶ በላይ መጽደቁን አስታውሰዋል።
አገር በቀል ችግኞች ላይ ትኩረት በማድረግ እየሰራ ሲሆን ለዚህ ዓመት አረንጓዴ አሻራ አገር በቀል ችግኝ የሚያባዛ ፕሮጀክት ማስተዋወቁንም ጠቁመዋል።
በዩኒቨርሲቲው ፕላንት ፊዚኦሎጂስት ዶክተር አስፋው ደጉ የተተከሉት አገር በቀል ችግኞች የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ተጽእኖ መቋቋም የሚያስችሉ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በዛሬው መርሃ-ግብር በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አራት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የሚያደርጓቸው ጥናትና ምርምሮችን በጋራ ለመሥራት የሚያችላቸውን ፎረም አቋቁመዋል።
የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና ፎረሙ ዩኒቨርሲቲዎች በተናጠል የሚያከናውኑትን ሥራ በተቀናጀ መንገድ በማስኬድ ለከተማዋ ልማት አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲዎች ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ለውጤታማነቱ በጥናትና ምርምር ማገዝ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ላይ የተገኙ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ለአረንጓዴ አሻራ ውጤታማነት በጥናትና ምርምር እንደሚያግዙ አረጋግጠዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአገር አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን በዚህ ዓመት "ኢትዮጵያን እናልብሳት" በሚል መሪ ሃሳብ ከ7 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል እቅድ ተይዟል።
ከዚህ ውስጥ 1 ቢሊዮኑ ችግኞች ለጎረቤት አገራት የሚሰጡ ይሆናል።