የኢትዮጵያዊያንን መብትና ጥቅም በመጋፋት የሌሎች አገሮችን ጥቅም ለማስከበር መሞከር ፍፁም ተቀባይነት የለውም- ቤተ ክርስቲያኗ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያዊያንን መብትና ጥቅም በመጋፋት የሌሎች አገሮችን ጥቅም ለማስከበር መሞከር ፍፁም ተቀባይነት የለውም- ቤተ ክርስቲያኗ
አዲስ አበባ ግንቦት 26/2013/ኢዜአ/ የኢትዮጵያዊያንን መብትና ጥቅም በመጋፋት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ተዕጽኖ በማሳደር የሌሎች አገሮችን ጥቅም ለማስከበር መሞከር ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ገለጸች።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አባቶች ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ የተለያዩ አገራት በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር መሞከራቸው ሉዓላዊነትን መዳፈር እንደሆነ ገልጸዋል።
የቤተ ክርስቲያኗ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል፤ ኢትዮጵያ የራሷ የተፈጥሮ ሃብት በሆነው የአባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም መብት በማንም ሊነፈግና ሊከለከል አይገባም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ስትገነባ ሌሎቹን ለመጉዳት ሳይሆን በድህነት የሚኖሩ ዜጎቿን ሕይወት ለመለወጥ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል።
ለግድብ ግንባታ ኢትዮጵያ ብድርና ድጋፍ እንዳታገኝ ተጽዕኖ ሲደረግባት መቆየቱን አውስተው ዜጎች በሚያዋጡት ገንዘብ በግንባታ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለይ የታችኞቹ የአባይ ተፋሰስ አገራት ኢትዮጵያ ወንዟን እንዳትጠቅም ተገቢነት የሌለው ስሞታ ከማቅረብ ይልቅ፤ በግድቡ ከሚነጨው ኃይል በጋራ ለመጠቀም ዝግጁ ቢሆኑ የተሻለ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ተናግረዋል።
የቤተክርስቲያኗ የጳጳሳት ጉባዔ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ዶክተር አባ ተሾመ ፍቅሬ፤ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ በምትሰራቸው ፕሮጀክቶች የማልማትና የሉዓላዊነት ጉዳይ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
አሜሪካና መሰል አገራት የተፋሰሱ አገሮች ወንዙን በጋራ መጠቀም እንደሚችሉ በመረዳት በኢትዮጵያ የመልማት መብት ላይ የሚሞከሩ ተግባራትን ማውገዝ አለባቸው ብለዋል።
"የኢትዮጵያዊያንን መብትና ጥቅም በመጋፋት የሌሎች አገሮችን ጥቅም ለማስከበር መሞከር ፍፁም ተቀባይነት የለውም" ነው ያሉት ዶክተር አባ ተሾመ።
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን የመጠቀም መብት የሚከለክሉ ኃይሎች ኢትዮጵያን በቅጡ ያልተረዱ ናቸው ሲሉም አባቶቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በገናና ታሪክና በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገች አገር እንደሆነች አንስተው ኢትዮጵያዊያን ሃብቷን ለመጠቀም በጋራ መቆም አለባቸው ብለዋል።
ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያንን መብት የሚያስከብር፣ ዕድገት የሚያረጋገጥና ለጎረቤት አገራትም የጋራ ጥቅም ይዞ ብቅ ያለ ፕሮጀክት መሆኑንም አብራርተዋል።
በአባይ ላይ ለዘመናት የቆዩ የበላይነት ጨዋታዎችንና የምዕራባዊያንን ግፊቶች ተቋቁሞ የዜጎችን የመልማት ጥያቄ መመለስ የኢትዮጵያ መንግስት ዋነኛ ኃላፊነት ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ክንውን አሁን ላይ ከ80 በመቶ በላይ መድረሱ ይታወቃል።