ኢትዮጵያዊያን የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመመከት የውስጥ አንድነትን ማጠናከር እንደሚኖርባቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመመከት የውስጥ አንድነትን ማጠናከር እንደሚኖርባቸው ተገለጸ
ሀዋሳ፤ ግንቦት 26/2013 (ኢዜአ) ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚያደርጉትን ሙከራ ለመመከት ዜጎች ልዩነትን ወደጎን በመተው አንድነታቸውን ማጠናከር እንደሚኖርባቸው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ/ኢዜማ / የሲዳማ ክልል ተወካይ አቶ እንግዳወርቅ አሰፋ እንዳሉት፤ አንዳንድ የውጭ ሀገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እያደረጉት ያለው ጣልቃ ገብነት ሀገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሀ ሙሌት በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዳይከናወን ለማድረግ ግብጽ እያካሄደችው ያለውን ዘመቻ በመቃወም ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው መቆም አለባቸው ብለዋል።
ያለችን ሃገር አንድ ናት ያሉት አቶ እንግዳወርቅ፤ የሀገሪቱን ሰላምና ዕድገት ለማስቀጠል ልዩነቶችን ወደጎን በመተው አሁን ላይ የገጠመውን ፈተና ለማለፍ ዜጎች ከመንግስት ጎን መቆም እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ፓርቲያቸው በአባሉና ደጋፊው ዘንድ ይህን ለማስረጽ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ /ኢሶዴፓ/ የሀዋሳ ተወካይ አቶ በለጠ ሱጌቦ በበኩላቸው፤ አሜሪካና ሌሎች ምዕራባዊያን በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት እያደረጉት ያለው ሙከራ እንደማይሳካ ተናግረዋል።
የሚገጥመንን የውጭና የውስጥ ፈተና ለማለፍ ሁሉም ዜጋ የሃገር ሉዓላዊነትና ህልውና ጉዳይ ማስቀደም አለበት ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን ይህን ለመመከት የውስጥ አንድነታቸውንና ሰላማቸውን ማስጠበቅ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያዊያን የዘመናት ቁጭት ለመሻር ያለምንም ልዩነት ያለንን በማዋጣት ግንባታው እየተካሄደ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በማጠናቀቅ ጠላቶችን ለማሳፈር ድጋፋቸውን በቁርጠኝነት ማጠናከር አለብን ብለዋል።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ የሲዳማ ክልል ተወካይ አቶ ተፈሪ ታፈሰ እንደተናገሩት፤ ከውጭ የሚደረገው ጣልቃ ገብነትን ለማክሸፍ የአሁኑ ትውልድ አብሮነትን በማጠናከር በሰከነ መንፈስ ለሃገር የሚጠበቅበትን ሊወጣ ይገባል።
ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ የውሃ ሃብት በፍትሃዊነት ለመጠቀም እያካሄደች ያለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌትና የእድገት ጉዞ ያልተዋጠላቸው ሃገራት የሚያካሂዱት ጣልቃ ገብነት ለመመከት መላው ኢትዮጵያዊ በአንድነት በመቆም የድርሻቸውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ምዕራባዊያን በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚያደርጉት ሙከራ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን የልማት ስራዎች በማስተጓጎል ተመጽዋች ሆና እንድትኖር በመፈለግ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ ናቸው።
ለዚህ ደግሞ በተለያየ ዘዴ ቅጥረኞችን በማስቀመጥና በመከፋፈል እነርሱ የሚሉትን ብቻ የምንፈጽም ደካሞች ሆነን እጅ እንድንሰጥ የሚደረግ ሙከራ ነው ብለዋል።
ዜጎች አንድነታችንን በማጠናከር ይህን ጊዜ ማለፍና የሃገራችንን ከፍታ ማረጋገጥ ይገባል ያሉት አቶ አብርሃም ብልጽግና የሃገር አንድነትና ሉዓላዊነትን ለማስከበር የሚያችሉ ተግባራትን በትኩረት እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።