የንግዱ ማህበረሰብ ለአገርና ለህዝብ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት አለበት ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የንግዱ ማህበረሰብ ለአገርና ለህዝብ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት አለበት ተባለ
ግንቦት 25/2013 (ኢዜአ) የንግዱ ማህበረሰብ ከትርፍ ባለፈ ለአገርና ለህዝብ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል አስገነዘቡ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ህግን አክብረው ለሰሩ ነጋዴዎችና ተቋማት እውቅናና ሽልማት አበርክቷል፡፡
ሚኒስትሩ በሽልማት አሰጣጡ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት የንግዱ ማህበረሰብ አገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በመረዳት ቅድሚያ ለአገርና ለህዝብ በመስጠት መሥራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
የንግዱ ማህበረሰብ ማትረፍም ሆነ የሚሰሩበትን ተቋም ማስፋፋት የሚችሉት አገርና ህዝብ ሲኖር በመሆኑ ጤናማ የሆነ የንግድ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡
በአንዳንድ ነጋዴዎች ላይ ምርት መደበቅ፣ ያለንግድ ፈቃድ መሥራትና ያለደረሰኝ ግብይት ማካሄድ እንደሚስተዋል ጠቅሰው ይህ አይነት አሠራር ህጋዊ ነጋዴውንና አምራቹን የሚጎዳ በመሆኑ በጋራ መከላከል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ለንግዱ ማህበረሰብ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የንግዱ ሥርዓት ሪፎርም መደረጉን፣ የኦላይን ግብይት መጀመሩ፣ እንዲሁም ከልማት ባንክ የብድር አገልግሎትና የመሥሪያ ቦታ መመቻቸቱን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
አገሪቱ የአለም የንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት አቶ መላኩ ይህ ውጤታማ እንዲሆን የንግዱ ማህበረሰብ አሠራሮችን ማዘመንና አገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል አለበት ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፤ ከተማ አስተዳደሩ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በማህበራት በኩል የተለያዩ ምርቶችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ስድስተኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ የንግዱ ማህበረሰብ በየአካባቢያቸው ህግን አክብረው በመሥራትና ህገ-ወጦችን በማጋለጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታህ የሱፍ በመዲናዋ የሚገኙ ነጋዴዎችና ተቋማት ህጋዊ የንግድ ሥርዓትን ለማስፈን፣ ገበያን ለማረጋጋት፣ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና በመንግሥት የልማት ሥራዎች ትብብር በማድረጋቸው ምክንያት ሽልማት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
በመዲናዋ የሚካሄደው የንግድ እንቅስቃሴ ዘመናዊ፣ ፍትሃዊና በውድድር ላይ የተመሰረተ ሆኖ ሸማቹን ማህበረሰብ ተጠቃሚ እንዲሆን የቁጥጥርና የክትትል ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
በዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ተከትሎ ባጋጠመው የኢኮኖሚ ቀውስ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
ቢሮው ህጋዊ ሆነው የሚሰሩትን እንደሚያበረታታ ሁሉ ህግን መሰረት አድርገው በማይሰሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ቢሮው በሁሉም ክፍለከተማ ህግን አክብረው ለሰሩ ነጋዴዎችና ተቋማት የሜዳሊያ ሽልማትና የምስር ወረቀት ሰጥቷል።
ሽልማት የተደረገላቸው የንግዱ ማህበረሰብና ተቋማት ህግን አክብረው ህዝብን በማገልገል ለሽልማት መብቃታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤ ሽልማቱ በቀጣይም ህግን አክብረው አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያበረታታቸው ተናግረዋል፡፡