ቀጥታ፡

የጌዴኦ ዞን ወጣቶች የውጭ ጣልቃ ገብነትን አወገዙ

ዲላ ፤ ግንቦት 25/2013( ኢዜአ) የጌዴኦ ዞን ወጣቶች በዲላ ከተማ ባካሄዱት ሰልፍ የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነትን በማውገዝ ተቃውሟቸውን ገለጹ።

በሰልፉ ምዕራባዊያን ከኢትዮጰያ ላይ እጃችሁን አንሱ፣ አንድነታችን ለግድባችንና ለአከባቢያችን፣ ለሰላም ዘብ በመቆም ለኢትዮጵያ እድገት የበኩላችንን እንወጣለን የሚሉ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ሙሉቀን ከበደ እንደተናገረው፤ የውጭ ጫናው በተሳሳተ ግንዛቤ ለአሸባሪው ህወሀት በመወገን   ሀገሪቱ ከተያያችው የእድገት ጎዳና ለማስውጣት የሚደረግ ጥረት ነው።

 እገዳ በመሪዎች ላይ መጣሉ ተቀባይነት የለውም ብላል።

ለሀገር አንድነትና ሰላም ዘብ በመቆም ኢትዮጵያ ስንዴ እየተሰፈረላት የምትኖር ሃገር ሆና እንዲትቀጥል የሚፈልጉ የውጭ ሃገራት ሴራ ለመከላከል የበኩሉን እንደሚወጣም ገልጿል።

ኢትዮጵያዊያን በዘር፣ ሃይማኖትና ቋንቋ ብንለያይም በሀገር ጉዳይ አንድ ነን ያለው ደግሞ ወጣት መንግስቱ ተክሌ ነው።

ድሃ መሆን ክብርን ማጣት አይደለም ያለው ወጣቱ ፤ በሀገር ጉዳይ ሁሉም በአንድነት መነሳት የግድ የሚልበት ጊዜ አሁን መሆኑን ለማሳየት በሰልፉ መሳተፉን ተናግሯል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽፈራው ቦጋለ ለሰልፈኞቹ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በተለየ የተደቀነባትን  ጫና ለመቋቋም በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ ሁለተኛው ዙር  የውሃ ሙሌትና መጪው ምርጫ በስኬት በማጠናቀቅ የውስጥ ጉዳይን  በራስ  መፈጸም እንደሚቻል ማሳየት  እንደሚገባ ተናግረዋል።

ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላም ከማስጠበቅ ባለፈ በአረንጓዴ አሻራና ሌሎች  ሀገራዊ ጉዳዮች ግንባር ቀደም ተሳፏቸውን በማጠናከር ለኢትዮጵያ እድገት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከየአቅጣጫው ለተደቀነብን ጫና ለሀገራችን እድገት በመስራት መልስ የምንሰጥበት ጊዜ አሁን ነው ያሉት ደግሞ የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዘማች ክፍሌ ናቸው።

የውጭ  ሃገራት ተላላኪዎች ሰላማችንን በማወክ  ምርጫውን ለማደናቀፍ የሚያደርጉትን ጥረት በተባበረ ክንድ መመከት ይገባናል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም