መገናኛ ብዙሃን የሳይበር ምህዳራቸውን ለመጠበቅ ያላቸው ዝግጁኑት አናሳ መሆን ለከፋ አደጋ ሊያጋልጣቸው እንደሚችል ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን የሳይበር ምህዳራቸውን ለመጠበቅ ያላቸው ዝግጁኑት አናሳ መሆን ለከፋ አደጋ ሊያጋልጣቸው እንደሚችል ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25/2013 ( ኢዜአ) መገናኛ ብዙሃን የሳይበር ምህዳራቸውን ለመጠበቅ ያለቸው ዝግጅኑት አነስተኛ መሆኑ ለከፋ አደጋ ሊያጋልጣቸው እንደሚችል የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስጠነቀቀ።
መገናኛ ብዙሃን በበኩላቸው የሳይበር ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ከኤጀንሲው አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግልን ይገባል ብለዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን "የመገናኛ ብዙሃን የሳይበር ተጋላጭነትና ሊወስዱ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች" በሚል መሪ ሀሳብ በጋራ ያዘጋጁት የውይይት መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
በመድረኩ "የሳይበር ደህንነትና የመገናኛ ብዙሃን ሚና" በሚል ርዕስ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው መገናኛ ብዙሃን የመረጃ ጤናማነት አስተማማኝ እንዲሆን ራሳቸውን ከሳይበር ጥቃት መጠበቅና መከላከል አለባቸው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት መገናኛ ብዙሃን ቴክኖሎጂን ለመጠቀም የሚሰጡትን ትኩረት ያህል የሳይበር ደህንነታቸውን ለመጠበቅ የሚሰጡት ትኩረት አነስተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።
የሳይበር ምህዳራቸውን ከመጠበቅ አንጻር መገናኛ ብዙሃን የሚያደርጉት ጥረት አነስተኛ በመሆኑ ያላቸው የዝግጁነት ማነስ ለከፋ ጉዳትና ጥቃት ሊያጋልጣቸው እንደሚችልና በዚህ ረገድ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ተለዋዋጭ፣ ውስብስብና ድንበር የለሽ የሆነው የሳይበር ምህዳር የዘመናችን ፈታኝ ተግዳሮት ነው ያሉት ዶክተር ሹመቴ ሳይበር ደህንነት በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃንም ይሄንኑ በመገንዘብ የሳይበር ደህንነት ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃን የሳይበር ደህንነት የስትራቴጂክ እቅዳቸው አንዱ አካል ማድረግ፣ የሰለጠነ የሰው ሃይል ቁጥርን መጨመርና የቴክኖሎጂ አቅምን ማጎልበት እንደሚጠበቅባቸውና ለዚህም የመገናኛ ብዙሃን አመራሮች ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ ያለው የሳይበር ደህንነት ንቃተ ሕሊና አነስተኛ በመሆኑ መገናኛ ብዙሃን በማህበረሰቡ ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙሃንን የሳይበር ደህንነት አቅማቸውን መገንባት የጋራ ትብብርና ጥረት የሚጠይቅ ስራ እንደሆነም አክለዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ መገናኛ ብዙሃን ከሳይበር ደህንነት ጋር የሚያስፈልጋቸውን ድጋፎች ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉ የመገናኛ ብዙሃን የስራ ሃላፊዎች መገናኛ ብዙሃን በበኩላቸው የሳይበር ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ከኤጀንሲው አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግልን ይገባል ብለዋል።
የሰው ሃይል አቅም ግንባታ፣ ስልጠናዎች፣ የሳይበር ጥቃትን መከላከል የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችና ስርዓቶች ድጋፍ እንደሚያሻቸው ገልጸዋል።
የመገናኛ ብዙሃን የሳይበር ደህንነት ዝግጁነት በየጊዜው ኦዲት በማድረግ ያላባቸውን ክፍቶች የመሙላት ስራ ማከናወን እንደሚገባም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ኢድሪስ ባለስልጣኑ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በመሆን መገናኛ ብዙሃን የሳይበር ደህንነት አቅማቸውን የሚያሳድግ ድጋፍ የሚያደርጉበት ሁኔታ እንደሚመቻች ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙሃን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር ያላቸውን ትብብርና ቅንጅት ማጠናከር በቀጣይ በትኩረት ተሰጥቶት የሚከናወን ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም የሳይበር ደህንነት ስጋት አስመልክቶ እ.አ.አ በ2020 ባወጣው ሪፖርት እ.አ.አ በ2021 የሳይበር ጥቃቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የስድስት ትሪሊዮን ዶላር ጉዳት እንደሚያደርሱ ትንበያውን ያስቀመጠ ሲሆን የሚደርሱ ጥቃቶች በአንድ ሰከንድ 190 ሺህ ዶላር ኪሳራ ያስከትላሉ ማለት ነው።
መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ለሳይበር ጥቃት ከፍተኛ ተጋላጭ ከሆኑ ዘርፎች አንዱ መሆኑንና በየጊዜው የተለያዩ ጥቃቶች እንደሚደርሱባቸው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ መረጃ ያመለክታል።
በሬዲዮ ጣቢያዎች ላይ የማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸውን መቆጣጠር፣ በቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ የመረጃ ቋታቸውን ማገት ፣የድረ-ገጽ ጥቃት፣ የመረጃ ስርቆትና ማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸውን መቆጣጠር የሚደርሱባቸው የሳይበር ጥቃቶች ናቸው።