ባዛርና አውደ ርዕዩ የልምድ ልውውጥና የገበያ ትስሰር እንድናደርግ ረድቶናል- የዝግጅቱ ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ባዛርና አውደ ርዕዩ የልምድ ልውውጥና የገበያ ትስሰር እንድናደርግ ረድቶናል- የዝግጅቱ ተሳታፊዎች
አምቦ፣ ግንቦት 25/ 2013 (ኢዜአ) በአምቦ ከተማ እየተካሄደ ያለው አውደ ርዕይና ባዛር የልምድ ልውውጥና የገበያ ትስስር የፈጠረላቸው መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ የዝግጅቱ ተሳታፊዎች ገለጹ።
“ከኮሮና ራሳችንን በመጠበቅ አምቦን በጋራ እናልማት!” በሚል መሪ ሀሳብ በአምቦ ከተማ በተከፈተው ባዛርና አውደ ርእይ ከ72 በላይ ኢንተርፕራይዞች እየተሳተፉ ነው።
ከተሳታፊዎቹ መካከል ከአዲስ አበባ የመጣው ወጣት አብዲ ሁሴን "ባዛሩ ምርታችንን ከመሸጥ ባለፈ ከሌሎች ኢንተርፕራይዞች ልምድ እንድንለዋወጥ አግዞናል" ብሏል፡፡
ከጓደፈኞቹ ጋር በመሆን በባዛሩ ላይ የወለል ምንጣፍ፣ አንሶላዎችና ብርድልብሶች ይዘው በመቀረብ ለሽያጭ ማቅረባቸውን ተናግሯል ።
በባዛሩ ላቀረቡት ምርት ገበያ ከማግኘታቸው ባለፈ ወደፊት ምርታቸውን ለመሸጥ ደንበኛ ማፍራት አንደቻሉ ገልጻል።
ከጅማ ከተማ የመጣው አሊዪ ሙሳ በበኩሉ በአውደ ርዕዩና ባዛሩ ላይ የጅማን የእንጨት ምርት ውጤቶችን በባዛሩ መሸጥና ማስተዋወቅ መቻሉን ተናግሯል፡፡
"ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ተነስቼ ለውጤት በቅቻለሁ" ያለው ወጣት አሊዪ አሁን በተሰማሰራበት የእንጨት ውጤቶች ንግድ ስራ ከ25 ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩንና ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማፍራቱን ጠቅሷል።
"ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ምርታችንን ከመሸጥ ባለፈ ከሌሎች ኢንተርፕራይዞች ልምድ ልውውጥ ለማድረግ አግዞኛል" ያለችው ደግሞ የኮስሞቲክስ ውጤቶች ይዛ ከጓደኞቿ ጋር በዝግጅቱ ላይ የተገኘችው ወጣት ውብ አለም ታደሰ ናት፡፡
እንዲሁም “ባዛሩ ላይ መሳተፌ በቀጣይ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ያግዘኛል” ብላለች።
"በባዛሩ የተሳተፍኩት በዋናነት ምርቶቼን ለማስተዋወቅና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ነው” ያለው ደግሞ ከአዲስ አበባ የመጣውና በቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁስ ንግድ የተሰማራው ወጣት ፈለቀ መንግስቱ ነው፡፡
ተሳታፊዎቹ እንዳሉት የአውደ ርዕዩና ባዛሩ መዘጋጀት ምርታቸውን በመሸጥ ከሚያገኙት ገቢ ባሻገር እርስ በእርስ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል ።
የአምቦ ከተማ አስተዳደር ንግድ ምክር ቤት ስራ እስኪያጅ አቶ ባጫ ዳቃ እንደገለፁት የአውደ ርዕዩና ባዛሩ ዓላማ ኢንተርፕራየዞች የገበያ ትስስር በመፍጠር የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ማገዝ ነው።
ባዛርና አውደ ርእይ ኢንተርፕይዞችና ማህበራት የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው፣ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉና ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ አስተዋጾ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
የቢቂልቱ ንግድ ፕሮሞሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ደጀኔ አበራ በበኩላቸው በአውደ ርዕዩና ባዛሩ ላይ የእንጨት ስራዎች፣ የአልባሳትና የኤሌክትሪክ ውጤቶች፣ የወለል ምንጣፎች፣ የቅባት ውጤቶችና ፕላስቲክ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ቀርበዋል።
ባዛርና አውደ ርእዩ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚሰበሰብ ተመላክቷል።
በቢቂልቱ ንግድ ፕሮሞሽንና በአምቦ ንግድ ምክር ቤት ትብብር ተዘጋጅቶ ከግንቦት 12 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በአምቦ ከተማ እየተካሄደ ያለው ባዛርና አውደ ርእዩ ነገ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።
ባዛርና አውደ ርእዩ ላይ ከ72 በላይ ኢንተርፕራይዞችና ማህበራት መሳተፋቸውና ከ30 ሺህ በላይ በሚሆኑ ሰዎችም መጎብኘቱ ተገልጻል።