ቀጥታ፡

ህዝቡ የውጭ ጫናን በመቋቋም የታላቁ ህዳሴ ግድብን ከዳር ለማድረስ በትብብር ሊሰራ ይገባል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25/2013 (ኢዜአ) ህዝቡ የውጭ ጣልቃ ገብነት እና ጫናን በመቋቋም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ከዳር ለማድረስ ከምንጊዜውም በላይ በአንድነትና በትብብር ሊቆም እንደሚገባ ተገለጸ።

በኢትዮጵያዊያን እየተገነባ የሚገኘውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እውን ለማድረግና የግድቡን ግንባታ ከዳር ለማድረስ ሌት ተቀን እየተሰራ ይገኛል።

ይህን ተከትሎ የተለያዩ የውጭ ጫናዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውም የሚታወቅ ነው።

እንዲህ ያሉ ጫናዎች ሲበራከቱ ህዝቡ በአንድነት በመቆም ግድቡን ከዳር ለማድረስ ሊተጋ እንደሚገባው የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች ለኢዜአ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን "ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር የዲፕሎማሲ የበላይነት እያሳየች መምጣቷ፤ ለግብጻዊያን የተዋጠላቸው አይመስልም" ይላሉ።

የግብጽ ስጋት ከግድቡ ግንባታ ባሻገር ይገባኛል በምትለው የውሃ ድርሻ ላይ ያላትን የበላይነት አጣለሁ የሚል መሆኑን ተናግረዋል።

ግብጽ አቋሟን በመቀያየር የግድቡ ግንባታ ከዳር እንዳይደርስ ከምትከተለው የፖለቲካ ሴራ አሁንም እንዳልተላቀቀች ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ኢትዮጵያን በውስጥ ጉዳዮቿ ለመፈተን በሚፈልጉ የውጭ አጀንዳ ፈጣሪዎች ሳይጠመዘዝ የአገሩን ጉዳይ በንቃት በመከታተልና የውስጥ አንድነትን በማጠናከር ሊቆም እንደሚገባ አክለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው ግድቡን እውን ከማድረግ ባሻገር ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ሊገነቡ ይገባል ብለዋል።

ነገር ግን የትኛውንም ጫና በመቋቋም የማትበገር ኢትዮጵያን ለማቆም በኢኮኖሚ የጠነከረች አገር መፍጠር ስለሚገባ ህዝቡ አንድነቱን ማስጠበቅ አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አበራ ወንድወሰን "አገር እውነት ከያዘና ህዝቡ በአንድነት ከቆመ የትኛውም ተጽእኖ በህዝቡ ላይ ሊያርፍ አይችልም'' ብለዋል።

"የህዳሴ ግድብ በራሱ በጎ የዲፕሎማሲ ተጽዕኖ የሚያመጣ በመሆኑ በቀጣይም ዛሬ ከኢትዮጵያ ጋር ያልቆሙት ሃሳባቸውን በማንሳት በትብብር የሚሰሩበት ወቅት ይመጣል" ነው ያሉት።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ አፈጻጸም 80 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ በመጪው የክረምት ወቅት ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም