ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን የሚደግፉበትና የዜግነት ግዴታቸውን የሚወጡበት ወቅት አሁን ነው - ባለሃብቶች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን በጋራ በመቆም አገራቸውን የሚደግፉበትና የዜግነት ግዴታቸውን የሚወጡበት ወቅት አሁን ነው ሲሉ የተለያዩ ባለሃብቶች ተናገሩ።

እየተካሄዱ ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች በወቅቱ እንዲጠናቀቁ ሁሉም በየመስኩ ኢኮኖሚውን በመደገፍ አገሪቱን ከተለያዩ ጫናዎች ማውጣት ይገባዋል ብለዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ባለሃብቶች መካከል በሰላም ባንክ መስራች ባለሀብት የሆኑት አቶ አርብሴ ጉግሳ እንደሚሉት "አሁን ኢትዮጵያዊያን 'ድር ቢያብር አንበሳ ያስር' የሚለውን ብሂል ተጠቅመው በጋራ በመቆም አገራቸውን የሚደግፉበትና የዜግነት ግዴታቸውን የሚወጡበት ወቅት ነው"።

በመሆኑም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የተጀመሩ የልማት ስራዎች የኢትዮጵያን ትንሳኤ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የትውልድና የአገር ሀብት በመሆናቸው ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅ ሁሉም ልዩነቱን አቻችሎ ጠንክሮ መስራት ይገባዋል ብለዋል።

"ያለችን አንዲት አገር ናት" የሚሉት አቶ አርብሴ መንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሕዝቡ በጋራ በመምከር የአገር ሕልውናን አስጠብቆ መጓዝ አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝቦ መስራት ይኖርበታል ይላሉ።

ሌላው የሰላም ባንክ መስራች ባለሀብት አቶ ቴዎድሮስ ይልማ በበኩላቸው ኢትዮጵያ አሁን የገጠሟት ተግዳሮቶች ራሷን ችላ ለመቆም የምታደርገውን ጥረትን እንድታፋጥን የሚያግዛት ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በራሷ መቆም እንደምትችል ማሳያ ከሆኑት ፕሮጀክቶች መካከል ከአፍሪካ በግዙፍነቱ የሚታወቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ነው።

"ይሕን መነሻ በማድረግ ሌሎችም የልማት ስራዎችን በራሳችን አቅም ለማጠናቀቅና ከተረጂነት መንፈስ ለመውጣት ቁርጠኛ አቋም ይዘን ከሰራን የማናሳካው ጉዳይ የለም" ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በበርካታ ተግዳሮቶች ተወጥራም ቢሆን የኢኮኖሚ እድገት ስታስመዘገብ የቆየች አገር መሆኗን አንስተዋል።

በመሆኑም አሁንም ከአገር ሕልውና የሚበልጥ ጉዳይ ባለመኖሩ አማራጩ ያለውን ሃብትና የሕዝቡን ጉልበት በመጠቀም የገጠሙንን ፈተናዎች ማለፍ ነው ብለዋል።

በሪል ስቴት ዘርፍ የተሰማሩት ባለሃብት አቶ አዲስ ገሰሰ እንደሚሉት ደግሞ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከቆሙ በተሰማራንበት መስክ ውጤት ለማምጣት የሚያዳግቱ ጉዳዩች እንደሌሉ በርካታ ማሳያዎች አሉ።

በዋናነትም ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተውና የተረጂነት መንፈስን በመታገል ሁሉም በየአካባቢው ያለውን ሃብት፣ ጉልበትና እውቀት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት ቢያደርግ ውጤት ሊመዘገብ ይችላል ብለዋል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት ከውጭም ከውስጥም እየታዩ ያሉትን ጫናዎች ተቋቁሞ ለማለፍ ወቅቱ የሚጠይቀው መደጋገፍና መደጋገፍ ብቻ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም