የውጭ ኃይል ጫናን ለመመከት የወታደራዊ ፖሊስ አባላትን አቅም ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ኃይል ጫናን ለመመከት የወታደራዊ ፖሊስ አባላትን አቅም ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣውን የውጭ ኃይል ጫና ለመመከት የወታደራዊ ፖሊስ አባላትን አቅም ማሳደግ እንደሚገባ የፌዴራል ህግና ፍትህ ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘካርያስ ኤርኮላ ይህን የተናገሩት ለወታደራዊ ፖሊስ አባላት መስጠት በተጀመረው ስልጠና መክፈቻ ላይ ነው።
የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ ደካማ መንግስት እንዲመሰረት ፍላጎት እያሳዩ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ወታደራዊ ፖሊሱ በወታደሩ ውስጥ የሚፈጠሩ ወንጀሎችን አነፍንፎ የማደን፣ ማስረጃዎችን የማሰባሰብ ፣ የመከላከያ አባላትን በስነ-ምግባር የማነፅ ሥራዎችን የሚሰራ ነው።
ስልጠናው እነዚህን ተግባራት በአግባቡ እንዲያከናውን የጎላ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል።
"በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ፣ የውጭ ጫናን የመመከትና ሌሎች ከሰላም ማስፈን ጋር የተያያዙ ትልልቅ ሥራዎች የሚሰሩበት ጊዜ ነው" ያሉት ዳይሬክተሩ እነዚህ ሥራዎች ጥንቃቄ እንደሚሹ አመልክተዋል።
የአገር ሉዓላዊነት የማስከበር፣ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥና ሌሎች ሥራዎች የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታና የውጭ ኃይሎች ጫናን በአግባቡ መረዳትን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
ስልጠናው እነዚህን እንዲያሟላ በማስረጃ ህግ ምዘና፣ በፀረ ሽብር ህግ፣ በወንጀል ስነ ስርዓት ህግ፣ በሰብዓዊ መብት ጥበቃና በታራሚዎች አያያዝ ላይ እንዲያተኩር መደረጉን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በስነ-ምግባሩ የታነፀ ጠንካራ ወታደራዊ ቁመና ያለው ሠራዊት ያላት አገር እንድትሆንና የሚመጣባትን ጫናዎች እንድትቋቋም የራሱ ሚና እንደሚኖረውም አመልክተዋል።
በመሆኑም በአገሪቱ ላይ የሚቃጣውን የውጭ ኃይል ጫና ለመመከት የወታደራዊ ፖሊስ አባላትን አቅም ማሳደግ የጎላ ሚና እንዳለው ነው ያስረዱት።
በመከላከያ ወታደራዊ ፖሊስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል ፍሰሃ ዋሴ በበኩላቸው "ስልጠናው ወታደራዊ ፖሊሱ የሚያከናውናቸውን ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ከማገዝ አኳያ ትልቅ ሚና ይኖረዋል" ብለዋል።
በተለይ አገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ ከህግ ማስከበሩ ጋር ተያይዘው የተነሱ ቅሬታዎች መኖራቸውን አስታውሰው፤ ወንጀል የሰሩ የመከላከያ አባላትን ወደ ህግ ለማምጣት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
"ወንጀል ሰርተው የጠፉ የመከላከያ አባላትን የወንጀል ማስረጃ ለማሰባሰብ፣ አድኖ ለመያዝና ለፍትህ አካላት አቅርቦ እስከማስቀጣት ያለውን የወታደራዊ ፖሊስ ሥራ ያፋጥናል" ብለዋል።
እንደ ኮሎኔል ፍሰሀ ገለጻ እነዚህ ሥራዎች ሲሰሩ ማንኛውም ወንጀለኛ የሰብዓዊ መብቱ በተጠበቀ መልኩ ወደ ፍትህ እንዲቀርብ ይደረጋል።
"ከወታደራዊ አለባበስና ስነ ምግባር ጀምሮ ያሉ ጉድለቶችን ባሉበት ከማረምና ከማስተካከል አኳያም ትልቅ ሚና ይኖረዋል" ብለዋል።
ስልጠናው ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት የሚሰጥ ሲሆን 64 የወታደራዊ ፖሊስ አባላት በስልጠናው እየተሳተፉ ይገኛሉ።