በሰኔ 16ቱ የቦምብ ጥቃት ተጠርጣሪ የጸጥታ አካላት ላይ ክስ ለመመስረት ተጨማሪ ጊዜ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በሰኔ 16ቱ የቦምብ ጥቃት ተጠርጣሪ የጸጥታ አካላት ላይ ክስ ለመመስረት ተጨማሪ ጊዜ ተጠየቀ
በሰኔ 16ቱ የቦምብ ፍንዳታ ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገባቸው በሚገኙ የፀጥታ አካላት ላይ ክስ ለመመስረት የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተጨማሪ 15 ቀናት ጠየቀ። የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ምርመራውን አጣርቶ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ መርቷል። በምርመራ ውጤቱ መሰረት አቃቤ ህግ በተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ለመመስረት ፍርድ ቤቱን የ15 ቀናት ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል። ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው የምርመራ ቡድኑና አቃቤ ህግ ስራቸውን በጋራ የሚሰሩ በመሆኑ በተሰጣቸው ጊዜ ውሰጥ ክስ መመስረት ሲገባቸው ባለመመስረታቸው በዋስትና ልንወጣ ይገባል ብለው ተከራክረዋል። የቤተሰብ አስተዳዳሪና ቋሚ አድራሻ ያለን በመሆኑ በተፈለግን ጊዜ መቅረብ ስለምንችል በዋስትና ልንወጣ ይገባልም ብለዋል። የዋስትና መብታችን መነፈጉ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን የሚጻረር ነው የሚል ቅሬታም አቅርበዋል። የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በበኩሉ ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት ቢሰጣቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ሊያሸሹ ስለሚችሉ ክስ እስኪ መሰረትባቸው ድረስ በዋስትና እንዳይወጡ ጠይቋል። በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የደረሰው የወንጀል አደጋ ጉዳቱ ከፍተኛና ትኩረት የሚያስፈልገው በመሆኑ የተገኙ የሰውና የሰነድ ማሰረጃዎችን በተገቢው መንገድ መርምሮና አጣርቶ ክስ ለመመስረት ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛል የሚል መከራከሪያም ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል። የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱም ዓቃቤ ህግ ከጠየቀው 15 ቀናት ውስጥ 10 ቀናት ፈቅዷል። በዚህም መሰረት አቃቤ ህግ ለነሀሴ 7 ቀን 2010 ዓ.ም መረጃዎችን በማጠናከር ክስ መስርቶ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ የጊዜ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን ተጠርጣሪዎቹም በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ወስኗል። በክስ መዝገቡ ላይ አንድ ተጨማሪ ተጠርጣሪ በመካተቱ የተጠርጣሪዎች ቁጥር 11 ደርሷል።