ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የቱሪዝም መዳረሻዎችንና መስህቦችን መረጃ ለቱሪስቶች የሚሰጥ መጽሐፍ እየተዘጋጀ ነው

ግንቦት 24/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን የቱሪዝም መዳረሻዎችንና መስህቦች መረጃ ለቱሪስቶች የሚሰጥ መጽሐፍ በተለያዩ የዩኒቨርሲቲ በምሁራን እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ።

የአገሪቱን የቱሪዝም መዳረሻዎች እና መስህብ ቦታዎች መረጃ ለመስጠት አጋዥ ነው የተባለው መጽሐፉ (ቱሪስት ጋይድ) ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተውጣጡ ባለሙያዎች አማካኝነት የተዘጋጀ ነው።

በመጽሐፉ ዙሪያ በቱሪዝም ሴክተሩ ከሚገኙ የተለያዩ አካላትና ሌሎች ባለሙያዎች ጋር ምክክር ተደርጎበታል።  

የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር እና የቱሪስት ጋይድ አዘጋጅ ቡድን መሪው ዶክተር ታከለ መርዕድ፤  ከዚህ ቀደም የነበረው ቱሪዝም አጋዥ መጽሐፍ በአብዛኛው በውጭ አገር ባለሙያዎች የተጻፈ እንደነበር ገልጸዋል።

በአዲስ መልክ  በዝግጅት ላይ የሚገኘው በፎቶና  በተሟሉ መረጃዎች የተሰነደና ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

ይኸውም በተለይ የአገሪቱን ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ኃይማኖታዊ መዳረሻዎችና መስህብ ቦታዎችን ለማስተዋወቅ እንዲሁም ለጎብኚዎች በቂ መረጃ በመስጠት ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያሏትን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ  ቅርሶችና ሃብቶችም በአግባቡ ተሰንደው እንዲቆዩ ያስችላል ነው ያሉት።

ቱሪስቶች ወደ አገር ወስጥ በሚመጡበት ወቅትም ስለሚጎበኟቸው ሥፍራዎችና መዳረሻዎች መረጃዎች በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ ያደርጋል ብለዋል።

በመጽሐፉ ከዚህ ቀደም የነበሩትን እና አዳዲስ የቱሪስት መስህቦችን በማካተት አገሪቱ አሁን ላይ ያሏትን የተፈጥሮ ሃብቶች  እንዲያሳይ ተደርጎ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያሳይ በመሆኑም ስለ ኢትዮጵያ የተጻፉና የሚነገሩ የተዛቡ አመለካከቶችን ለማስተካከል እንደሚረዳ ተናግረዋል።

በርካታ ያልታወቁና ያልታዩ ሃብቶቿን በማስተዋወቅ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ አዲስ እይታን ይዞ እንደሚመጣ ታምኖበታልም ብለዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎችም አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች መጽሐፉ ቱሪስቶች ወደ አገር ውስጥ በሚመጡበት ወቅት ስለሚጎበኙት ሥፍራ እንዲያውቁ ለማስቻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

መጽሐፉ ታትሞ ለተጠቃሚዎች ከዋለ በኋላ ወቅቱን ባገናዘበ ሁኔታ በየጊዜው እየተሻሻለ መውጣት እንዲችል መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

መጽሐፉ በበቂ ሁኔታ በፎቶ የተደገፉ እና ይበልጥ ገላጭ ሆኖ እንዲቀርብ በዘርፉ ከተሰማሩ አስጎብኚ ድርጅቶችና ሌሎች ባለሙያዎች ጋር መረጃዎችን የማቀናጀት ሥራ መጠናከር እንዳለበትም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም