በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት የተገኙ ውጤቶች ድህነትን ማሸነፍ እንደሚቻል ማሳያዎች ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት የተገኙ ውጤቶች ድህነትን ማሸነፍ እንደሚቻል ማሳያዎች ሆነዋል
ግንቦት 24/2013 (ኢዜአ) በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት የተገኙ ውጤቶች ድህነትን ማሸነፍ እንደሚቻል ማሳያዎች መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
"ሁሌም ለስኬት እንተጋለን" በሚል መሪ ሃሳብ 6ኛው ሀገር አቀፍ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የእውቅና መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ በሰው ልጅ ህይወት ላይ አተኩሮ በሚሰራው በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት የተገኙ ውጤቶች ድህነትን ማሸነፍ እንደሚቻል ማሳያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለስራ ክብርና ዋጋ የሰጡ ዜጎችም ኑሯቸው ትርጉም ባለው ሁኔታ እየተለወጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም ዘርፉ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ምሩቃንና ከስደት ተመላሽ ዜጎችን በልዩነት ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
የዘርፉ ስኬት ሀገራዊ ባለሃብቶች ማፍራት ያስቻለ ቢሆንም በርካታ ያልታዩ ስራ አጥ ዜጎች በመኖራቸው ወደ ዘርፉ ማቀላቀል እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።
መንግስት ባመቻቸው የድጋፍ ስርዓት አልፈው ድህነትን መሻገርና ለስኬት ለበቁ ተሸላሚዎችም እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ፤ የስራ እድል ፈጠራ የአመለካከት ለውጥን የሚጠይቅ ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሰርቶ ለመለወጥ ጽኑ እምነትና ብርታት በማሳደር ወደ ተግባር መለወጥ መቻል ከሚፈልጉት ግብ ለመድረስ የሚያስችል ጉዳይ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ አገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመንደፍ ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው ያሉት ደግሞ የፌደራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ናቸው።
ለዚህም ከድህነት ወለል በታች የሆኑ የከተማ ነዋሪዎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ መንግስት ሰፊ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ ከተማ ግብርና፣ አገልግሎትና ንግድ ዋና ዋና የስራ እድል የተፈጠረባቸው ዘርፎች እንደሆኑ ተመላክቷል።
በአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፍ የሚፈጠሩ የስራ መስኮችም የዜጎችን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ ለአገር ኢኮኖሚያዊ እድገት የማይናቅ ሚና እየተጫወቱ መሆኑ ተገልጿል።
የስራ እድሎቹ ለስኬት እንዲበቁ የስልጠና፣ የፋይናንስ፣ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን፣ የመስሪያ ቦታና መሸጫ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
በመርሃ ግብሩ 106 ኢንተርፕራይዞች፣ 80 የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ሞዴል ኢንተርፕራይዞች፣ 60 የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችና ባለሙያዎች፣ ሶስት ድጋፍ የሚያደርጉ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት እና ሶስት የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ተቋማት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
በከተማ ግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት የስራ ዘርፎች ባለፉት አስር ወራት ለ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች ስራ ለመፍጠር ታቅዶ ለ1 ነጥብ 52 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን መረጃዎች ያሳያሉ።