ቀጥታ፡

በአባይ ዙሪያ በሚሰሩ ጥናትና ምርምሮች ወንዙ የኢትዮጵያዊያን ህልውና መሆኑን የሚያሳዩ ሊሆኑ ይገባል --የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ስለሺ

ግንቦት 24/2013 (ኢዜአ) ምሁራን በአባይ ዙሪያ በሚሰሯቸው ጥናትና ምርምሮች ወንዙ የኢትዮጵያ ህዝብ ህልውና መሆኑን የሚያሳዩ መሆን ይገባቸዋል ሲሉ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ አስገነዘቡ።

“አንድ ድምፅ አንድ አቋም ለታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን መሆን” በሚል መሪ ሀሳብ የምሁራን ኮንፈረንስ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ የውሃ፣ መሰኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንዳሉት ኢትዮጵያዊያን ድህነትን ለማሸነፍ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ከግብ የማድረስ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡

የአባይ ወንዝ ምንጭ በሆነችው ኢትዮጵያ 26 ሚሊዮን የሚገመተው ህዝቧ የንጹህ መጠጥ ውሀ እንዲሁም 65 ሚሊዮን የሚሆነው ደግሞ የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ አለመሆኑን ተናግረዋል።

"የህዝቡን ችግሮች ለመፍታትና መጪውን ትውልድ ተጠቃሚ ለማድረግ ግድቡን ከዳር ማድረስ የአማራጭ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ ነው "ብለዋል፡፡ 

ግድቡን ማጠናቀቅ የሀገርን ዕድገት ሊያፋጥኑ የሚያስችሉ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች በማቋቋም ተገቢውን ሃይል እንዲያገኙ ከማስቻል በላይ የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮችን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር እንደሚያስችል ገልጸዋል።

"ግብጽና ሱዳን እኔ ብቻ ልጠቀም በሚል እሳቤ የቅኝ ግዛት ውሎችን በኢትዮጵያ ላይ ለመጫን ቢጥሩም ኢትዮጵያ አንጡራ ሀብቷን ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ለመጠቀም የሚሹትን አትቀበልም" ብለዋል።

"በተለይም ምሁራን በአባይ የኢትዮጵያ ህዝብ ህልውና መሆኑን የሚያስገነዝብ ጥናትና ምርምር በማድረግ የበኩላቸውን የሚወጡበት ጊዜ አሁን ነው" ሲሉ አመልክተዋል፡፡

ምሁራን በማንኛውም ሁኔታ በአባይ ዙሪያ በሚያከናውኗቸው ጥናትና ምርምሮች ወንዙ የኢትዮጵያዊያን ህልውና መሆኑን ማሳየት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

"የኢትዮጵያ ህዝብም አንድነቱን በማጠናከር የሚደረግበትን ተጽዕኖ በማክሸፍ ለግድቡ ግንባታ ዘብ መቆም አለበት" ሲሉ አሳስበዋል።

"የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው ግብፅና ሱዳን እስካሁን ድረስ ያለ ከልካይ ሲጠቀሙ ለነበሩበት የኢትዮጵያ ውሃና አፈር ካሣ መክፈል ይገባቸዋል" ብለዋል፡፡

"አንዲት ላም ወተት ልትሰጥ የምትችለው መኖ በአግባቡ ሲቀርብላት ነው" ያሉት ዶክተር አረጋዊ ግብፅና ሱዳን አባይን ብቻቸውን ለመጠቀም ከመባዘን ይልቅ ለአባይ ዘላቂ ልማት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

"ሽብርተኛው ህወሃትና መሰሎቹ ጫካ ሆነው ግብፅና አሜሪካ በሚያደርጉላቸው ድጋፍ አንድነታችንን በመበታተን የግድቡን ግንባታ ለማምከን እያሴሩ በመሆናቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ይበልጥ አንድነቱን ማጠናከር ይገባዋል" ብለዋል።

"ወቅቱ የሀገራችንን መፃኢ ዕድል የምንወስንበት በመሆኑ የአባይን ግድብ በማጠናቀቅ የኢኮኖሚ አቅማችንን ማጠንከር ያስፈልጋል " ብለዋል።

ምሁራን ስለአባይ ያልተነገሩ ዕውነታዎችን በማጥናት ድምጻቸውን  በዓለም አቀፍ መድክ ሊያሰሙ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚበታትን ሳይሆን አንድነቱን ይበልጥ የሚያጠናክር ፕሮጀክት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው በውሃው ዘርፍ ምሁራንን በማፍራት የበኩሉን ሲወጣ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአባይ ወንዝ ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዳትሆን የሚደረገውን ተጽዕኖ በውሃ ሳይንስ ዕውቀት ማክሸፍ እንደሚገባ አስገንዘበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም