ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ጫናዎች አጥብቀው እንደሚቃወሙ የአሶሳ ነዋሪዎች ገለጹ

አሶሳ ፤ ግንቦት 24/2013 (ኢዜአ) ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ማንኛውም ጫና አጥበቀው እንደሚቃወሙ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የአሶሳ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋረዎቹ የውጭ ጫናን በመቃወም ዛሬ በአሶሳ ከተማ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡

በተቃውሞ ሰልፉ ከተሳተፉት መካከከል ወይዘሮ ዝሁር ከማል በተለይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት፤ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራብያውያን በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚደርጉት ጫና ተገቢነት የለውም፡፡

የኢትዮጵውያን አንድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተጠናከረ መጥቷል ያሉት ወይዘሮ ዝሁር፤ የትኛውም የውጭ ጫና ሃገሪቱን ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት እንደማይገድበው ተናግረዋል፡፡

በተለይም የህዳሴው ግድብ ለኢትዮጵያውያን ህልውና ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፕሮጀክቱን ከዳር ለማድረስ ወሳኙ ጉዳይ አንድነታችንን ማጠናከር ነው ብለዋል፡፡

አሁን ከውጭ እየተደረገብን ያለው ጫና ምንም አያሰጋንም ፣ የኢትዮጵያን አቋምም አይቀይርም ያሉት ደግሞ ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ አቶ እንቁ ወርቁ ናቸው፡፡

ይልቁንም ጫናው ውስጣዊ አንድነታችንን ያጠናክርልናል ብለዋል፡፡

በህብረ ብሔራዊነት ተነስተን ሠላማችን መጠበቅና በተሰማራንበት የስራ መስክ ውጤት ማስመዝገብ አለብን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እየደረሰብን የሚገኘው የውጭ ጫናም ይህንኑ እንድንፈጽም ያስገድዳል በማለት አብራርተዋል፡፡

ወይዘሮ ጠይባ አባስ በበኩላቸው፤ ፡ግድባችን ማንም እንዲነካው አንፈልግም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በየትኛውም ተጽዕኖ የኢትዮጵያ እድገት እንደማይደናቀፍ ገልጸው፤ የግድቡ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እና ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የውጭ  ጫና ሳይበግረው እንዲከናወን በሚደረገው እንቅስቀሴ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

በተቃውሞ ሰልፉ የተሳተፉትም ይህን እውነታ ለመላው ዓለም ህብረተሰብ ለማሳወቅ ነው ብለዋል፡፡

ወይዘሮ ራሄል ተስፋው የተባሉ ነዋሪ ደግሞ ኢትዮጵያ የሶስት ሺህ ዓመት ታሪክ ያላት ታላቅ የጀግኖች አባቶች ሃገር እንደሆነች ገልጸዋል፡፡

የጎረቤት ሃገራት መንግስታት ቢቻል ከእኛ ተስማምተው ቢሰሩ ካልሆነ በራሳችን ፕሮጀክት ላይ ፈቃጅም ከልካይል ሊሆኑ እንደማይችሉ ሊያውቁ ይገባል ብለዋል፡፡

ግድቡም ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል፣ ምርጫውም ይከናወናል፣ ኢትዮጵያም ትቀጥላልች ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ምዕራባውያን ከተራ ማስፈራራት ተቆጥበው ከኢትየጵያ ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲ እንዲያጠናክሩ፣ የውስጥ ጠላቶችም እጃቸውን ሰብስበው ይህችን ታላቅ ሃገር አብረን ብናስከብር መልካም ነው ብለዋል፡፡

የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኡመር መሃመድ ለሰልፈኞቹ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷን በማንም ሳታስደፍር የኖረች ታላቅ ሀገር እንደሆነች ገልጸዋል፡፡

ይህም በተለይ ለጥቁሮች የነጻነት ፈር ቀዳጅ እንድትሆን አድርጓታል ብለዋል፡፡

የነጻነቷ ሚስጥር ደግሞ ዜጎቿ የውስጥ ችግሮች እያሉባቸው ጭምር በሃገራቸው ጉዳይ አንድ ሆነው በመነሳት የውጭ ጠላትን ማሳፈራቸው እንደሆነ ከንቲባው አስታውሰዋል፡፡

ዛሬም ለአሜሪካ እና ለየትኛውም የውጭ ጫና የሚንበረከክ ዜጋ እንደሌለ የገለጹት አቶ ኡመር በተለይ ወጣቶች የሃገራቸውን አኩሪ ታሪክ እንደሚያስቀጥሉ የሚተማመኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ለፍጻሜ የተቃረበው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንዲጠናቀቅ ነዋሪዎች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም