ቀጥታ፡

የሀይማኖት ተቋማት የኢትዮጵያን ዘመን ተሻጋሪ መልካም እሴቶች ማስቀጠል ይገባቸዋል- ጉባኤው

ጎንደር ግንቦት 24/2013 (ኢዜአ) የሃይማኖት ተቋማት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብርና በጋራ በመስራት ዘመን ተሻጋሪ መልካም እሴቶቻች ሊያስቀጥሉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ አቀረበ፡፡

ጉባኤው በሰላም፣ በአብሮነት፣ በሃይማኖትና በብሄር ብዝሃነት ላይ የሚመክር ውይይት በጎንደር ከተማ እየተከሄደ ነው።

የጉባኤው ምክትል ጠቅላይ ጸሃፊ ሃጂ መስኡድ አደም በድረኩ ላይ እንደተናገሩት ዘመናት የዘለቀውን የመከባበርና የመደጋገፍ አኩሪ ባህል ይበልጥ በማበልጸግ ኢትዮጵያን ከገጠማት ፈተና ማሻገር ይገባል።

የሰላም እሴትን በመገንባት፣ ግጭትን በመፍታት እንዲሁም አብሮነትንና አንድነትን በማጠናከር የህዝቦችን የጋራ እሴቶች በማስቀጠል በኩል የሃይማኖት ተቋማት ድርሻ የላቀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የመልካም አሴቶቻችን መገለጫ የሆኑ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች በህብረተሰቡ ዘንድ ይበልጥ ሰርጸው እንዲገቡ በማድረግ በኩል የሃይማኖት ተቋማት የጀመሩትን እንቅስቃሴ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

"በሀገራችን የሚስተዋሉ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች የሰውን ልጅ ታላቅነትና ክቡርነትን የማይመጥን ኢ_ሰብአዊ ድርጊት ከመሆኑም በላይ በሁሉም ሃይማኖቶች ተቀባይነት የሌለው ከታሪካችንና ከባህላችን ያፈነገጠ ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የሃይማኖት አውድ የሌላቸውና የሃይማኖታዊ ምግባር ሚዛን የጎደላቸው ኢ_ሰብአዊ ድርጊቶችን በማስቆም ዘላቂ ሰላም በማምጣት በኩል መንግስት፣ ህዝብና የሃይማኖት ተቋማት ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡  

ጉባኤው በሰላምና እርቅ ጉዳዮች እንዲሁም ሀገርና ህዝብን አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶች ከፍተኛ ጥፋትና ውድመት ሳያስከትሉ በሰላማዊ መንገድ በእርቅ የሚፈቱበትን መንገድ በማመቻቸት በኩል በርካታ ተግባራት ሲያከናውን መቆየቱን  አስታውቀዋል፡፡

''የሃይማኖት ተቋማት የሰላም እሴቶችን በመገንባት፤ አብሮነትንና ተፈጥሮአዊ የሆነውን ብዘሃነትን በመቀበልና በማክበር ግንባር ቀደም ሚና አላቸው'' ያሉት ደግሞ ጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ ናቸው፡፡

"የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሁሉንም ሃይማኖቶች በአንድ ጥላ ስር በማሰባሳብ በሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ  በጋራ  በማሰለፍ አብሮነትና አንድነት እንዲጠናከር ድጋፍ እያደረገ ያለ ተቋም ነው" ብለዋል፡፡

በመድረኩ "የግጭት አያያዝና አፈታት ሂደት" በሚል ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር የፀጥታ አማካሪ አቶ ከፍአለ እሱባለው በበኩላቸው የሃይማኖት ተቋማት ግጭቶችን በእርቀ ሰላም በመፍታት በኩል ያካበቱትን ልምድ አሟጠው ሊጠቀሙ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

"የሃይማኖት ተቋማት ዘመን ተሻጋሪና በጊዜ ያልተገደበ ህልውናና ተልእኮ አላቸው" ያሉት አማካሪው በሰላም ግንባታ ዙሪያ ሲያበረክቱት የቆዩት አስተዋጽኦም ድርሻው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

''ጊዜው የምንተባበርበትና አንድ የምንሆንበት፤ ኢትዮጵያንም ከውስጥና ከውጭ አፍራሽ ጠላቶችዋ የምንታደግበት ወቅት ነው'' ያሉት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊ ሊቀ ትጉሃን ስጦታው አለባቸው ናቸው፡፡

በመድረኩ በሰላም እሴት ግንባታ፣ በሃይማኖትና ብሄር ብዝሃነት አያያዝ እንዲሁም በግጭት አፈታትና ቅድመ ጥንቃቄ ጉዳዮች ዙሪያ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በባለድርሻዎች ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው፡፡

ለሁለት ቀን በሚቆየው የምክክር መድረክ የጉባኤው ከፍተኛ አመራሮች ከባህርዳርና ከጎንደር የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም