ቀጥታ፡

ኤጀንሲው በጡረተኞች የሚነሳውን ቅሬታ መፍታት እንዳለበት ተጠቆመ

አዲስ አበባ ግንቦት 24 / 2013/ኢዜአ/ አዲስ አበባ፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመንግስት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ በጡረተኞች በኩል የሚነሳውን ቅሬታ መፍታት እንዳለበት ጠቁሟል፡፡

ይህን ያሳሰቡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሆኑት ወ/ሮ እምዬ ቢተው የኤጀንሲውን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም በገመገመበት ወቅት ነው፡፡
ኤጀንሲው በተለይ ከክፍያ መዘግየት ጋር ተያይዞ ጡረተኞች ለሚያነሱት ቅሬታ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዳለበት ነው የተናገሩት፡፡ኤጀንሲው ያለበትን የሰው ኃይል እጥረት በመፍታትና አዳዲስ ለሚቀጠሩ ሠራተኞች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና በመስጠት ያከናወናቸውን ተግባራት እና አሰራሩን ለማዘመን የሚያስችሉ አሰራሮች መዘርጋቱን ወ/ሮ ዕምዬ በጥንካሬ ከጠቀሷቸው መካከል ይገኙበታል፡፡

ወደ ኤጀንሲው መግባት የነበረበት የጡረታ ውዝፍ መዋጮ እንዳልገባ የገለጹት ወ/ሮ ዕምዬ፤ እየተንከባለሉ የመጡ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት የኤጀንሲው አዋጅና ደንብ መጽደቅ እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳባ ዓርዓያ በበኩላቸው በቋሚ ኮሚቴው የተጠቀሱት ችግሮች መኖራቸውን አንስተው፣ ችግሮቹን ለመፍታት ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ አሰራሮችን በመዘርጋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ኤጀንሲው 187 ሺህ ለሚጠጉ የጡረተኛ ተገልጋዮች ክፍያ በባንክ በኩል እንዲስተናገድ መደረጉንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም