ቀጥታ፡

የአፍሪካ ነጠላ የኤሌትሪክ ኃይል ገበያ ተግባራዊ መሆን ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24/2013 ( ኢዜአ) የአፍሪካ ሕብረት በዓለማችን ትልቁ የኤሌትሪክ ኃይል ገበያ ነው ያለውን የአፍሪካ ነጠላ የኤሌትሪክ ኃይል ገበያ ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ።

ነጠላ ገበያው የአፍሪካ አገራት በኤሌትሪክ ሃይል ያላቸውን ትስስር ማጠናከርና ገቢ የሚያገኙበትን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጿል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ የስራ ክፍል የአፍሪካ ነጠላ የኤሌትሪክ ኃይል ገበያ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ከነገ በስቲያ በበይነ መረብ አማካኝነት ያካሄዳል።

የአፍሪካ ነጠላ የኤሌትሪክ ኃይል ገበያ እ.አ.አ በ2019ኙ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ማዕቀፍ ስር የተቀናጀ አህጉራዊ የኤሌትሪክ ኃይል ገበያ የመፍጠር ትልምን በማሳካት የአፍሪካን የኢነርጂ ዘርፍ ማሻሻል አላማ ያደረገ ነው።

ገበያው በአፍሪካ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች ፣የቢዝነስ ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች ደህንነቱ የተጠበቀ፣ዘላቂነት ያለው ፣አስተማማኝ የሆነ፣ተወዳዳሪና ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ የኤሌትሪክ ኃይል በተሻለ ሁኔታ እንዲያቀርቡ የማድረግ ግብ አለው።

ገበያውን የመፍጠር ጉዞ የተጀመረው እ.አ.አ በ2015 የአፍሪካ ሕብረት በአፍሪካ ያለውን የኤሌትሪክ ሃይል የሕግ ማዕቀፎችን ለማጣጣምና ለማዋሃድ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር በመተባበር ተግባራዊ ሲያደርገው በነበረው መርሃ ግብር አማካኝነት ነው ።

በስራ ክፍሉ አስተባባሪነት የአውሮፓ ሕብረትና የሕብረቱ የቴክኒክ ድጋፍ ማዕቀፍ መርሃ ግብር(ታፍ) ባለሙያዎች ላለፈው አምስት ዓመት የፖሊሲ ሰነዶች ፣ፍኖተ ካርታና አስተዳደራዊ መዋቅር ሲያዘጋጁ ነበር ተብሏል።

በባለሙያዎቹ የተዘጋጁት ሰነዶችና የመዋቅር አደረጃጀቶች በአፍሪካ ሕብረት ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች(ሬክስ)፣የጋራ የኤሌትሪክ ሃይል ገበያ(ፓወር ፑል) በሚሰሩ አገራትና የፓን አፍሪካ የኢነርጂ ተቋማት ማረጋገጫ አግኝተዋል።

እ.አ.አ በ2021 በየካቲት ወር በተካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ሰነዶቹና መዋቅሩ እንዲጸድቅ መደረጉም የሚታወስ ነው።

የአፍሪካ ነጠላ የኤሌትሪክ ኃይል ገበያ ለአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት የኢነርጂ ደህንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ዘላቂነት ያለውና ተወዳዳሪ የኤሌትሪክ  ኃይል አቅርቦት እንደሚፈጥር ታምኖበታል።

ከ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ሕዝብ በላይ በሚኖርበት አፍሪካ ነጠላ የኤሌትሪክ ኃይል ገበያ የዓለማችን ትልቁ ግብይት መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ገልጿል።

የአፍሪካ ነጠላ የኤሌትሪክ ኃይል ገበያን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት በይፋ እንደሚያስጀምሩት የአፍሪካ ሕብረት መግለጫ ያመለክታል።

በማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት፣የአፍሪካ ሕብረትና የአውሮፓ ሕብረት የኢነርጂ ኮሚሽነሮች፣የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢነርጂ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ንግግር እንደሚያደርጉ የወጣው መርሃ ግብር ያሳያል።

በመርሃ ግብሩ የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት የአፍሪካ ነጠላ የኤሌትሪክ ኃይል ገበያ ያላቸውን ድጋፍ ይሰጣሉ።

ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ(አይኢኤ) እ.አ.አ በ2019 የአፍሪካ ኢነርጂ አስመልክቶ ባወጣው ትንበያ በአፍሪካ ያለው የኢነርጂ ፍላጎት በሰዓት 700 ቴራ ዋት እንደሆነ ገልጿል።

እ.አ.አ በ2040 በአፍሪካ ያለው የኢነርጂ ፍላጎት አሁን ካለበት በ50 በመቶ እንደሚጨምር ሪፖርቱ ያመለክታል።

ከዓለም የሕዝብ ብዛት 17 በመቶውን የሚሸፍነው የአፍሪካ አህጉር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የኢነርጂ ኢንቨስትመንት ድርሻ 4 በመቶ ብቻ እንደሆነ የዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ(አይኢኤ) አስታውቋል።

አፍሪካ እ.አ.አ በ2040 በዓመት ለኢነርጂ የምታወጣውን ኢንቨስትመንት ወደ 120 ቢሊዮን ዶላር ማድረስ እንደሚጠበቅባት የሚገልጸው ኤጀንሲው የአፍሪካን የኢነርጂ ፍላጎት ለማሟላት በቀጣዮቹ ሁለት አስርት ዓመታት በአህጉሩ ያለውን የታዳሽ ኃይል ምንጭ በስፋት መጠቀም እንደሚያስፈልግ ምክረ ሀሳቡን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም