ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የግብጽን ተለዋዋጭ አካሄድ መመከት የሚያስችል ዲፕሎማሲያዊ ቁመና መፍጠር እንዳለባት ተጠቆመ

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2013/ኢዜአ/ ኢትዮጵያ፤ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል ግብፅ እየተከተለችው ያለውን ተለዋዋጭ አካሄድ ለመመከት የሚያስችል ዲፕሎማሲያዊ ቁመና መፍጠር አለባት ሲሉ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የአረብኛ ቋንቋ መምህር ኡመር መኮንን ተናገሩ።

በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶች የአባይ ጉዳይን ልዩ የዲፕሎማሲ ትኩረት አድርገው መስራት እንደሚገባቸውም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ 86 በመቶ የአባይ ምንጭ ብትሆንም የስሟ መጠሪያ ከመሆን ባለፈ ሳትጠቀምበት ዘመናት ነጉደዋል።

አባይ ኤሌክትሪክ እያመነጨልኝ ይፍሰስ በማለት የዛሬ 10 ዓመት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን እውን ለማድርግ የመሰረት ድንጋይ ስታኖር ግብፆች “ምን ሲሆን” በማለት ሲያሻቸው በክስ ሲሞቃቸው ደግሞ በማስፈራራት እነሆ እስካሁንም ዘልቀዋል።

አሁን ላይ የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ተከናውኖ ለሁለተኛው ዙር ዝግጅት እየተደረገ ቢሆንም ግብፅና ሱዳን “የአባይን ልጅ ውሃ ይጥማት” የሚለውን ውትወታቸውን ቀጥለዋል።

በ1960 ግንባታው ተጀምሮ በ1971 የተጠናቀቀው፤ በናይል ወንዝ ላይ የተገነባው የአስዋን ግድብ ለግብፅ የመስኖና የቱሪዝም ሃብት ከመሆኑ መተጨማሪ 2 ሺህ 100 ሜጋ ዋት የኤሌክተሪክ ሃይል በማመንጨት አገልግሎት ይሰጣል።

ከዓለማችን ሰውሰራሽ ሃይቆች መካከል በግንባር ቀደምትነቱ የሚጠቀሰውና በ5 ሺህ 250 ስኩየር ኪሎ ሜትር ላይ የተንጣለለው የናስር ሃይቅም የግብፅ ሌላኛው የቱሪዝም፣ የመስኖና የዓሳ ሃብት ምንጭ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።

ግብፅ ከወንዙ ይህንን ሁሉ ጥቅም በማገኘት ላይ ብትሆንም የኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጫነት ልጠቀም ላለችው ኢትዮጵያ “አታደፍርሽብኝ” አይነት የተንኮልና ምቀኝነት ተግባሯን አጠናክራ ቀጥላለች። 


የታለቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት እውን መሆኑን ተከትሎም ግብጻውያን ዲፕሎማቶች፣ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ያለምንም ልዩነት ኢ-ፍትሃዊ የሆነ አቋማቸውን ዓለም እንዲቀበላቸው እየሰሩ ነው።

በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የአረብኛ ቋንቋ መምህርና "በግድብ ዙሪያ አረቦች ስለ ኢትዮጵያ ምን ይላሉ?" በሚል የግብጽ ሚዲያዎችን ዳሰሳ በማድረግ የሚታወቁት ኡመር መኮንን፤ የግብጽ ሊሂቃን ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ በማባላት የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል እየሰሩ መሆኑን ይናገራሉ።

በግብጽ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ የፖለቲካና ስትራቴጂክ ጥናት ማዕከሎችም "በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመግባት እንዴት ግድቡን ማስቆም ይቻላል" በሚሉ ሃሳቦች መጠመዳቸውን ነው የገለጹት።

የግብፅን ሴራ ለመመከት "እኛስ ለኢትዮጵያ ምን መስራት አለብን?" የሚለው ጥያቄ በሁሉም አካላት ዘንድ መነሳት አለበት ይላሉ መምህሩ።
ግብፆች በሀገራቸውም ሆነ በውጭ በጋዜጠኞችና ዲፕሎማቶች የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ቀን ከሌት እየሰሩ በመሆኑ ይህንን በመመከት የዲፕሎማሲ የበላይነት ለመያዝ ኢትዮጵያ ብዙ ስራ ይጠብቃታል ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ሊከናወን መሆኑን ተከትሎም የውጭ ጫናዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን የጠቅሰው፤ የውሃ ሙሌቱን በስኬት ማከናወን በግድቡ ዙሪያ የሚነሱ ችግሮች እንዲፈቱ ያደርጋል ነው ያሉት።

ከዚህ ጎን ለጎን የግብጽን ተለዋዋጭ አካሄድ የሚመክቱ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች መከናወን እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻር በተለያዩ አገራት ኢትዮጵያን የወከሉ ዲፕሎማቶች በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን እውነታ ለዓለም ህዝብ ማስረዳት አለባቸው ብለዋል።

ግድቡ በተለያዩ ሀገራት ከተገነቡ የሃይል ማመንጫ ግድቦች ጋር አብሮ የሚጠቀስ መሆኑን የገለጹት የዩኒቨርሲቲ መምህሩ ግብጽ ጉዳዩን ዓለም አቀፋዊና አረባዊ ይዘት እንዲኖረው ጥረት እያደረገች መሆኑን አብራርተዋል።

ግብፅ በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ እ.ኤ.አ. የ1929 እና የ1959 ዓ.ም የፈረምኩት ተጠቃሚ የሚያደርገኝ የቅኝ ግዛት ውል ሊከበርልኝ ይገባል የሚለውን አቋሟን አሁንም አልቀየረችም።

ግብጽ በ1929 የተፈረመው የቅኝ ግዛት ስምምነት ቀጣይነት እንዲኖረው ስትሻ ሱዳንም በ1959 ከግብጽ ጋር የተፈራረምኩት የአባይ ውሃ አጠቃቀም ስምምነት ይቆይልኝ የሚል አቋም አላት።

በዚህ ስምምነት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ባለመካተታቸው በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1999 ሁሉን የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ያጠቃለለ ስምምነት ለመድረስ የሚረዳ አንድ እቅድ ቢቀርብም ግብጽና ሱዳን እቅዱን ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።


ለውሃው ፍትሃዊ ተጠቃሚነት "ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ" የሚለው የኢትዮጵያ ጽኑ አቋም ዲፕሎማሲያዊ ድል እያስገኘ መሆኑን የጠቀሱት መምህሩ ይሄው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሚገጥሟትን የትኛውንም አይነት የውጭ ጣልቃ ገብነቶች ከአፍሪካውያን ወንድሞች ጋር በመሆን መመከት እንደሚገባትም ገልጸዋል።


የ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ አፈጻጸም አሁን ላይ 80 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ የፊታችን ክረምት ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም