ፈተናዎችን በድል በማለፍ የሃገሪቱ ብልፅግና እናሳካለን- ብልፅግና ፓርቲ - ኢዜአ አማርኛ
ፈተናዎችን በድል በማለፍ የሃገሪቱ ብልፅግና እናሳካለን- ብልፅግና ፓርቲ
ወልዲያ፤ ግንቦት 23/2013 ( ኢዜአ) አሁን የገጠሙን ፈተናዎችን በድል በማጠናቀቅ የሃገራዊ የብልፅግና ጉዞ እናሳካለን ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር ሰይድ ኑሩ ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ የድጋፍ ሰልፍና ዕጩዎችን ለህዝብ የማስተዋወቅ ስነ-ስርዓት ዛሬ በሰሜን ወሎ ዞን በሃብሩ ወረዳ መርሳ ከተማ ተካሄዷል።
ፓርቲውን ወክለው በሃብሩ ወረዳ ለተወካዮች ምክር ቤት እጩ ሆነው የቀረቡት ዶክተር ሰይድ ኑሩ በስነ ስርዓቱ ወቅት እንዳሉት፤ ብልፅግና ሀገርን በሁለንተናዊ መንገድ ለመለወጥ እየተጋ ያለ ፓርቲ ነው።
ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖ ሚከናወን ትክክለኛ የዴሞክራሲ በር የሚከፈትበት ታሪካዊ ምርጫ ነው ብለዋል።
''ከዚሁ ጎን ለጎን ለብልፅግና መሰረት የሆነው የህዳሴው ግድብ ለሀገራችን ብዙ ጠላቶችን የፈጠረ ቢሆንም በሃገሩ ሉአላዊነት የማይደራደረውን የኢትዮጵያ ህዝብ በመያዝ ችግሮቹን ሁሉ በድል እንወጣቸዋለን'' ሲሉ ገልጸዋል።
ምርጫውና ሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እንዳይሳካ አልመው የተነሱ ሃይሎችን ሴራ አክሽፎ በድል በማጠናቀቅ ለሃገራዊ ብልፅግና መሰረት የሚጣልበት ወቅት መሆኑን ዶክተር ሰይድ ተናግረዋል።
የሃሳብና አመለካከት ልዩነት ተፈጥሯዊ በመሆኑ ሕዝቡ በልዩነት ላይ በአግባቡ መከራከርን መፍራት እንደሌለበት ጠቅሰው፤ የሃሳብ ልዩነት ግጭትን ማስከተል እንደሌለበት አመልክተዋል።
ብልጽግና ሕዝቡ ከጥቂት አመራሮች ጋር ታግሎ ያመጣውን ለውጥ በማስቀጠልና ጁንታውን ድባቅ በመምታት የአንበሳውን ድርሻ መወጣቱንም ጠቅሰዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ ውጤቶች ዳር ለማድረስና ሃገሪቱ ወደ ተደላደለ ብልፅግና ለማምጣት ህዝቡ ብልፅግናን እንደሚመርጥ ጠይቀዋል።
ዶክተር ሰይድ ኑሩ፤ በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙ ናቸው።
''በዚህ ዓመት በብዙ ውድድርና ፈተና ታጅቦ የሚካሄደው ምርጫ ለሀገር ልማትና ብልጽግና ይጠቅማል'' ያለው ደግሞ የመርሳ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሲራጅ መሀመድ ነው፡፡
''ምርጫው ልክ እንደ እግር ኳስ ጨዋታ ደቂቃው ሲጠናቀቅ ሰላም ተባብለው እንደሚለያዩ ሁሉ በምርጫውም አሸናፊና ተሸናፊ እንኳን ደስ አለህ ተባብለው የሚለያዩበት መሆን አለበት'' ብሏል።
ምርጫው ማሸነፍም ሆነ መሸነፍ እንዳለ ሆኖ ሰላማዊና ያለምንም እንቅፋት መከናወን እንዳለበት ጠቅሶ፤ ለውጤታማነቱም የበኩሉን እንደሚወጣ ገልጿል።
ወጣት ጻድቃን ጥላሁን በበኩሏ፤ የወቅቱን የምዕራባውያንን ተጽእኖ ለመቋቋም ሀገራዊ አንድነትን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ገልፃ፤ የሀገሪቱን ሉአላዊነትን ለማስከበር የድርሻዋን አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደምትጥር ተናግራለች።
በትውውቁ ስነ-ስርዓት በአካባቢው ያሉ የብልፅግና አባላትና ደጋፊዎች ለፓርቲው ያላቸው ድጋፍ ባሰሟቸው መፈክሮች ገልጸዋል።