በትምባሆ ላይ የወጣውን አስገዳጅ መመሪያ በማስተግበርና በመቆጣጠር ሂደት ውስንነቶች አለ- የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
በትምባሆ ላይ የወጣውን አስገዳጅ መመሪያ በማስተግበርና በመቆጣጠር ሂደት ውስንነቶች አለ- የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን
ግንቦት 23 ቀን 2013 (ኢዜአ) በትምባሆ ላይ የወጣውን አስገዳጅ መመሪያ በማስተግበርና በመቆጣጠር ሂደት ውስንነቶች መኖራቸውን የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ በኢትዮጵያ ለ29ኛ ግዜ በዓለም አቀፍ ደግሞ ለ34ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን አስመልክቶ ከጤና ሚኒስቴርና ከአጋር አካላት ጋር መግለጫ ሰጥቷል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሔራን ገርባ እንዳሉት ትምባሆ በውስጡ ከ7 ሺህ በላይ ኬሚካሎችን መያዙን ጠቁመው፣ ከእነዚህ ውስጥ 69 በመቶ ያህሉ ለተለያዩ የካንሰር ህመሞች መንስኤ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ከ1 ቢሊዮን በላይ አጫሾች እንደሚገኙ ጠቁመው "ከእነዚህ ውስጥ 7 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚሆኑት ከትምባሆ ጋር በተያያዘ በሚከሰት የጤና እክል ህይወታቸውን ያጣሉ" ብለዋል።
በኢትዮጵያም እንዲሁ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች የትምባሆ ምርት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው ዳይሬክተሯ ያስታወቁት።
ችግሩን ለመቀነስ ተቋማቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በ2011 ዓ.ም በትምባሆ ላይ የወጣውን አስገዳጅ መመሪያና ለማስተግበር ጥረት ቢደረግም አሁንም ውስንነቶች አሉ ብለዋል።
በማህበረሰቡ ዘንድ ግንዛቤ በመፍጠር ሂደትም እንዲሁ።
"አብዛኛው አጫሾች የሚመርጧቸው ቦታዎች ምግብ ቤቶች፣ መኖሪያ ቤቶች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መሆናቸው ደግሞ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል" ብለዋል።
በእዚህም የማያጬሱ ሰዎች ከሚያጬሱ ሰዎች ባልተናነሰ ሁኔታ ለካንሰር፣ ለመተንፈሻ አካላት ችግር፣ ለስኳር፣ ለጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ እና ለልብ ሕመም የሚጋለጡ መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡና ቅንጅታዊ አሰራርን እንዲያጎለብቱ አስገንዝበዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው የትምባሆ ምርቶች ቁጥጥርን በተመለከተ የወጣው አዋጅ 11/12 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጸደቀ ሦስት ዓመታት መቆጠሩንን አስታውሰዋል።
"በመመሪያው መሰረት በትምባሆ ምርት ላይ የቀረጥ ጭማሪ ከማድረግ ባለፈ በፓኬቱ ላይ ለጤና ጎጂነቱ እንዲገለጽ የተደረገበት እርምጃ አበረታች ቢሆንም አሁንም በመመሪያው ሊፈተሹና ቁጥጥር ሊደረባቸው የሚገባ ጉዳዮች አሉ" ብለዋል።
ትምባሆ ህዝብ በሚሰበሰብበት እንዲሁም በበርና መስኮት አካባቢ 10 ሜትር ዙሪያ እንዳይጨስ የሚከለክለው ድንጋጌ ሰፊ ክፍተትና ችላ የተባለ ጉዳይ መሆኑን አስታውሰዋል።
"ይህም በትምባሆ ዙሪያ የሚሰሩ አበረታች ሥራዎችን የሚያከሽፍና በሚፈለገው ልክ ውጤት እንዳይመጣ አድርጓል" ብለዋል ዶክተር ሊያ።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሚያጨሱና በትምባሆ ሳቢያ የጤና እክል ያጋጠማቸው ሰዎች ላይ በጽኑ የሚበረታና ለሞትም የሚዳርግ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
"የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ የሚመለከታቸው አካላት ከባለስልጣኑና ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመቀናጀት መመሪያውን ለማስተግበር የራሳቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባል" ብለዋል።
የዘንድሮው የዓለም ትምባሆ የማይጬስበት ቀን ''ትምባሆ ያጨሳሉ? እንግዲያውስ ቆራጥ ይሁኑ'' በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚከበረው።