ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የአሸናፊ ዋንጫውን ተረከበ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ግንቦት 23/2013የ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋንጫውን ተረከበ።

ከግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የማጠቃለያ መርሃ ግብር ዛሬ ተጠናቋል።

የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር መዝጊያ ስነ ስርዓት ትናንት እንዲካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረ ቢሆንም የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ህዝባዊ ሰልፍ ምክንያት ወደ ዛሬ መዘዋዋሩ የሚታወስ ነው።

ዛሬ በ18ኛ ሳምንት ከሊጉ መርሃ ግብርና ከውድድር ዓመቱ የመጨረሻ ጨዋታ አስቀድሞ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ መሆኑን ያረጋገጠው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከመከላከያ ያደረጉት ጨዋታ በመከላከያ 32 ለ 30 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱንም ተከትሎ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ28 ነጥብ የውድድር ዓመቱን በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ፤ በአንጻሩ መከላከያ በ26 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

ከትናንት በስቲያ በተደረገ የ18ኛ ሳምንት ጨዋታ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ፌደራል ፖሊስን 17 ለ 16 በማሸነፍ በ24 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

የ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የድል ዋንጫውን ዛሬ ተረክቧል።

ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን በ2010 ዓ.ም የሊጉ አሸናፊ እንደነበር የሚታወስ ነው።

የቂርቆስ ክፍለ ከተማው ሙሉጌታ ግርማ ኮከብ አሰልጣኝ፣ የቂርቆስ ክፍለ ከተማው መሐመድ ከድር ኮከብ ተጫዋችና ፌደራል ዳኛ ኤርሚያስ ደሳለኝ ኮከብ ዳኛ በመሆን የተመረጡ ሲሆን ልዩ የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግን ዘንድሮ የተቀላቀለው ባህር ዳር ከተማ የጸባይ ዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።

የፕሪሚየር ሊጉ ተሳትፊ ክለቦችና ውድድሩ ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ ላደረጉ ግለሰቦች፣ ተቋማትና ክልሎች የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር፣ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍትሕ ወልደሰንበት ፣ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል ረዲና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመዝጊያ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።

የዘንድሮ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በዘጠኝ ክለቦች መካከል ሲካሄድ የቆየ የነበረ ቢሆንም ጎንደር ከተማ "በበጀት ችግር" ምክንያት ራሱን ከውድድሩ ውጪ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

ቡታጅራ ከተማ "በበጀት ችግር" እንዲሁም መቐለ ሰብዓ እንደርታ በዘንድሮው ውድድር ላይ አልተሳተፉም።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በ2009 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን መከላከያ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ እስካሁን በተካሄዱ ውድድሮች አሸናፊ የሆኑ ክለቦች ናቸው።

የ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠ ሲሆን ውድድሩም ያለ አሸናፊ እንዲሰረዝ መደረጉ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም