ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየሪ ሊግ አክሲዮን ማህበር ያሳለፈውን ውሳኔ እናከብራለን- ስፖርት ኮሚሽን

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ግንቦት 23/2013 የኢትዮጵያ ፕሪሚየሪ ሊግ አክሲዮን ማህበር፤ የተጫዋቾችን ወርሃዊ ደመወዝ አስመልክቶ ያሳለፈውን ውሳኔ እናከብራለን ሲል የፌደራል ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ።

በ2011 ዓ.ም የፕሪሚየሪ ሊግ ክለቦች ተጫዎቾች ወርሃዊ ደመወዝ ከፍተኛው ገንዘብ 50 ሺህ ብር እንዲሆን መወሰኑ ይታወቃል።

በወቅቱ ስፖርት ኮሚሽን ክለቦችን በማወያየት የገንዘቡ መጠን በክለቦቹ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም በተጫዋቾች በኩል ቅሬታ ሲፈጥር ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየሪ ሊግ አክሲዮን ማህበር ትናንት ባካሄደው ጉባኤ በተጫዎቾች ወርሃዊ ክፍያ ላይ ገደብ መቀመጡ ክለቦችንና ተጫዎቾችን ለተለያዩ ችግሮች እየዳረገ ነው በሚል የደመወዝ ጣሪያ ገደቡ እንዲነሳ ተወስኗል።

በጉባኤው የደመወዝ ጣሪያ ገደቡ በመቀመጡ እንደችግር ተብለው ከተነሱት መካከል አብዛኞቹ ክለቦች በመመሪያ የተቀመጠውን ገንዘብ መጠን የውል ወረቀቱ ላይ እንጂ በውስጥ ለውስጥ ድርድር ተጨማሪ ገንዘብ እየከፈሉ መሆኑ አንዱ ነው።

ይህም መንግስት ማግኘት ያለበትን ግብር እንዲያጣ ምክንያት እየሆነ መምጣቱ በመድረኩ ተነስቷል።

ከዚህ በተጨማሪ የተጫዋቾች ዝውውር ፕሮፌሽናል አካሄድ እንዳይከተል አድርጓል።

በእዚህም በተጫዋቾችና ክለቦች መካከል በየጊዜው አለመግባባት እንዲፈጠርና ውድድሩ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ነው በጉባኤው የተገለጸው።

ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ፕሪሚየሪ ሊግ አክሲዮን ማህበር ባካሄደው ጉባኤ ለተጫዎቾች የተቀመጠው የ50 ሺህ ብር ደመወዝ ጣሪያ ገደብ እንዲነሳ ተወስኗል ።

አብዛኞቹ ክለቦች በራሳቸው ገቢ ሳይሆን በመንግስት በጀት የሚተዳደሩ በመሆኑ የብዙዎች የስፖርት ቤተሰቦች ጥያቄ የነበረው ይህን ውሳኔ የፌደራል ስፖርት ኮሚሽን እንዴት ይቀበለዋል? የሚል ነበር።

የፌደራል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኤሊያስ ሽኩር፤ መንግስታዊ አካሉ ስፖርትን ለማገዝ ስትራቴጂ ማውጣት እንጂ እንደዚህ አይነት መመሪያ የማውጣት፣ ውድድር የመምራት ስልጣኑ የፌዴሬሽኖች ነው ብለዋል።

"ከዚህ በፊት የተጫዋች የደመወዝ ጣሪያ ገደብ ሲቀመጥ ስፖርት ኮሚሽን ክለቦች እንዲወያዩበት መድረክ የሚመቻችበት እድል የመፍጠር እንጂ ውሳኔው የክለቦች ነበር" ሲሉም አስታውሰዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ፕሪሚየሪ ሊግ አክሲዮን ማህበር በፕሪሚሪሊግ ተጫዎቾች ላይ የነበረው የደመወዝ ጣሪያ ገደብ እንዲነሳ ያሳለፈውን ውሳኔ ኮሚሽኑ ያከብራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም