ቀጥታ፡

በምርጫ ሂደቱ ፓርቲዎች የሰብአዊ መብቶችን በማክበር በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ መንቀሳቀስ ይገባቸዋል - ኢሰመኮ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ግንቦት 23/2013 በምርጫ ሂደቱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰብአዊ መብቶችን በማክበር በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ መንቀሳቀስ ይገባቸዋል ሲሉ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ።

ኮሚሽኑ በምርጫ ሂደት ሊከበሩ ይገባቸዋል ብሎ ያዘጋጃቸውን ባለ 6 ነጥብ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳ ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያይቷል።

በአጀንዳዎቹ ተጨባጭ የሰብአዊ መብቶች እርምጃዎች ቃል ኪዳን፣ ለሰብአዊ መብቶች በቁርጠኝነት መቆም፣ ከግጭት ቀስቃሽና ከጥላቻ ንግግር መታቀብ የሚሉ ይገኙበታል።

አጀንዳዎቹ በምርጫ ሂደቱ የሚያጋጥሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመቀነስ ፓርቲዎች፣ የፌደራልና የክልል የጸጥታ አካላት ሊያተኩሩባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በዝዝርዝር አስቀምጠዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ የተዘረዘሩ ነጥቦች የቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ በምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎች ሁሉ በምርጫ ሂደቱ የሰብአዊ መብቶችን በማክበር በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ መንቀሳቀስ አለባቸው ብለዋል።

በገዥው ፓርቲ የሚፈጸሙ ጥሰቶችን ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደሚያወግዙት ሁሉ በአባላቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው የሚፈጸምን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሊከላከሉና በአጥፊዎች ላይ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል ብለዋል።

ፓርቲዎች በምርጫው ካሸነፉ በተጨባጭ ሊያሻሽሉ የሚችሉባቸው የሰብአዊ መብት አጀንዳዎቻቸውን ለህዝብ ቃልኪዳን በመስጠት ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ ንግግሮችና ተግባራት ሊቆጠቡ ይገባልም ነው ያሉት።

የፖለቲካ ምህዳሩ አሁን ላይ በአንፃራዊነት የተሻለ ቢሆንም ከሰብአዊ መብቶች ጥሰት ነጻ አለመሆኑን ጠቅሰው ሁሉም ፓርቲዎች ችግሩን መፍታት አለባቸው ብለዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተዘረዘሩት ነጥቦች አስፈላጊ መሆናቸውን በመጥቀስ ለተግባራዊነታቸው የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጨጠዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ፤ ኮሚሽኑ በምርጫው ሂደት ሊከበሩ ይገባቸዋል ብሎ ያስቀመጣቸውን ነጥቦች ወቅታዊነትና አስፈለጊነት ገልጸዋል።

ፓርቲዎች በሙሉ በምርጫ ሂደቱ ሰብአዊ መብቶችን አክብረው በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ የፈረሙት የቃል ኪዳን ሰነድ መቀመጡን አውስተው ለተግባራዊነቱ እንዲተጉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በቅድመ ምርጫ፣ ምርጫና ድህረ ምርጫ ጋር በተያዘዘ የሚነሱ የሰብአዊ መብት ሁኔታዎች ላይ ክትትል በማድረግ ተገቢ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዜጎች በምርጫ ሂደቱ መሳተፋቸውን ማረጋገጥና ሌሎች ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።

ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ሙሉ ለሙሉ በተጠናቀቀባቸው አካባዎች የድምጽ መስጫ ቀን ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም መሆኑ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም