ዕጩ ተወዳዳሪዎች በሀገር ሠላምና ዴሞክራሲ ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል -ቦርዱ - ኢዜአ አማርኛ
ዕጩ ተወዳዳሪዎች በሀገር ሠላምና ዴሞክራሲ ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል -ቦርዱ
ሀዋሳ ግንቦት 23/2013 (ኢዜአ) በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚሳተፉ ሴት ዕጩ ተወዳዳሪዎች በሀገር ሠላምና ዴሞክራሲ ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብና ሲዳማ ክልሎች በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሚሳተፉ ሴት ዕጩ ተወዳዳሪዎች በምርጫ ሕግ ማዕቀፍና በሥርዐተ-ፆታ እኩልነት ላይ ያተኮረ ስልጠና ዛሬ በሀዋሳ ከተማ መስጠት ጀምሯል፡፡
በቦርዱ የሥርዓተ ፆታና ማህበራዊ አካታችነት ዘርፍ ሥራአስኪያጅ ወይዘሮ መድኃኒት ለገሰ በወቅቱ እንዳሉት ሴቶች በህበረተሰብ ውስጥ ባላቸው ማህበራዊ መስተጋብር በሀገር ደረጃ አወንታዊ ተፅዕኖዎችን የመፍጠር ሚናቸው ከፍተኛ ነው።
በተለይ አሁን ላይ ሀገሪቱ 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ እንደመሆኗ ሴቶች በምርጫው በተወዳዳሪነት መቅረባቸውና በውሳኔ ሰጪነት ቦታ መቀመጣቸው እንደ ሀገር ዘላቂ ሠላምን የማስፈን ብሎም ለውጥ የማምጣት ሚናቸው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
ሴቶች የፓርቲያቸውን መስመር በመጣስ ጭምር የድርድርና የሠላም በር በመክፈት አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ የቻሉ መሆናቸውን ዓለም አቀፍ ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ ጠቅሰዋል።
በቦርዱ የተዘጋጀው የሥልጠና አላማም በምርጫው የሚወዳደሩ ሴቶች ሚናቸውን በመገንዘብ በሀገር ሠላምና ዴሞክራሲ ግንባታ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ግንዛቤና አቅም ለመፍጠር መሆኑን አስታውቀዋል።
በምርጫው የሚወዳደሩ ሴቶች በፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ ሌላው የስልጠናው አላማ መሆኑን አመልክተዋል።
ብልጽግና ፓርቲ በዲላ ከተማ ምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት ያቀረባቸው ዕጩ ተወዳዳሪ ወይዘሮ ፀሐይ ወራሳ "ሴቶች በሀገር ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፍ የሚፈለገውን ለውጥ ለማስመዝገብ የሚያስችል ውጤታማ መንገድ ነው" ብለዋል።
ፓርቲያቸው በደቡብ ክልል በዕጩነት ያቀረባቸው ሴቶች በተለያየ የሥራ መስክ ውጤታማ የሆኑና ማህበረሰባቸውን በማስከተል የተሻለ መስራት የሚችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
"ሴት ዕጩ ተወዳዳሪዎች በፖለቲካው መስክ ስንሳተፍ ተጋግዘን ሀገርን በሠላም የማስቀጠል ኃላፊነትን ይዘን ነው" ያሉት ወይዘሮ ፀሐይ ሥልጠናው ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንደሚያግዛቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የወላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ወህዴግ/ በሶዶ ዙሪያ ምርጫ ክልል አንድ ለክልል ምክር ቤት ያቀረባቸው ዕጩ ተወዳዳሪ ወይዘሮ ሙሉነሽ ሶርሳ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
በተለይ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሴቶች ተሳትፉ በእጅጉ ማደጉን እንደታዘቡ የተናገሩት ወይዘሮ ሙሉነሽ ከየትኛውም ፓርቲ ቢሆን የሴቶች ተሳትፎ መጨመሩ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ በእኩልነት የመወሰን ዕድላቸውን የሚያሰፋው መሆኑን አመልክተዋል።
ሴቶች በተፎካካሪ ፓርቲዎች ውስጥ ለመሳተፍ ውስጣዊና ውጫዊ የአመለካከት ጫና ቢኖርባቸውም ፓርቲያቸው በአባልነትም ሆነ በዕጩ ተወዳዳሪነት ለማካተት ጥረት ማድረጉንና ለቁጥር የበዙ ባይሆኑም ያሉትን በብቃትና በኃላፊነት ተልዕኳቸውን እንዲወጡ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሥልጠናው በሥርዐተ-ፃታ ፅንሰ-ሀሳቦች፣ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ህግጋት፣ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት ውስጥ በተካተቱ የሴቶችና አካል ጉዳተኞች የፖለቲካ ተሳትፎ የህግ ማዕቀፎች እንዲሁም በምርጫ ህግጋት ዙሪያ ያተኮረ መሆኑ ተመላክቷል።
ለሁለት ቀን በሚቆየው ሥልጠና በደቡብና ሲዳማ ክልሎች በሚገኙ ምርጫ ክልሎች ፓርቲዎችን ወክለው ለህዝብ ተወካዮችና ክልል ምክር ቤቶች ለውድድር የቀረቡ ሴት ዕጩዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡ ፡