ቀጥታ፡

ምርጫ ቦርድ በመራጮች ትምህርት ላይ ከተሠማሩ የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ ግንቦት 23/2013/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመራጮች ትምህርት ላይ ከተሠማሩ የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት ጋር መወያየቱን አስታወቀ።

በውይይቱ ወቅት የቦርዱ አመራር አበራ ደገፋ (ዶ/ር) ቦርዱ የመራጮች ትምህርት ለሚያስተምሩ 167 የሲቪክ ማኅበራት ፍቃድ መሰጠቱን ገልጸዋል።
በዚህም ፈቃድ የተሰጣቸው ማኅበራት በሰጡት የመራጮች ትምህርት አማካኝነት ካርድ የወሰዱ ዜጎች ቁጥር መሻሻሉን ጠቁመው፤ ለዚህም ከፍተኛ አክብሮት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ማኅበራቱ በቀጣይ በሚከናወነው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ዜጎች በንቃት እንዲሣተፉና ድምፃቸውን በነፃነት ለፈለጉት ዕጩ እንዲሰጡ ማሰተማር አሰፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
በድምፅ አሰጣጥ ሂደት በመራጮች መሳሳት የሚባክን ድምፅ እንዳይኖር በመራጮች ትምህርት አሰጣጥ ላይ የተሰማሩ የሲቪክ ማህበራት ትምሀርቱን በተገቢ መስጠት እንደሚኖርባቸው፤ እንዲሁም በድኅረ ምርጫ ሁኔታዎች ሰላማዊ እንዲሆን ዜጎች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አጽንዖት ሰጥተዋል።የውይይቱ ተሣታፊዎች በማስተማር ወቅት የፋይናንስ ውሥንነት ፣ የአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ሁኔታ፣ ከቦርዱ የተሰጣቸውን የዕውቅና ባጅና ደብዳቤ ቢያሳዩም የመንግሥት የፀጥታ አካላት በማስተማር ወቅት ከበላይ አካል አልተነገረንም በሚል ክልከላ እያደረጉባቸው በሥራቸው ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል እንደፈጠሩባቸው አሳውቀዋል።
አበራ (ዶ/ር) አበራ በተነሱ ጥያቄዮች ላይ በሰጡት ማብራሪያ ማኅበራቱ የሚያሠማሯቸው አስተማሪዎችን ገለልተኛነት ከማረጋገጥ አንጻር በቂ ክትትል ማድርግ፣ መራጩ ኅብረተሰብ የድምፁን ዋጋ በአግባቡ እንዲረዳና የመራጭነት ካርዱም ከግለሰቡ ሊለይ እንደማይገባ፤ እንዲሁም በድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ የሚኖሩትን እያንዳንዱ ቅደም ተከተል በዝርዝር መራጩን ማሳወቅ እንዳለበት አብራርተዋል።
በድምፅ አሰጣት ሂደትም የድምፅ መስጫ ወረቀት በሚበላሽበት ጊዜ የሚኖረውን የአወጋገድ ሥርዓትም ጭምረው ያብራሩት ሲሆን የፀጥታ አካላትን ተባባሪነት አስመልክቶ ለተነሡ ጥያቄዎችም መልስ ሰተዋል።
በዚህም ቦርዱ ለሲቪክ ማኅበራቱ ሕጋዊነት የሰጠው የዕውቅ ሰርተፍኬት፣ ባጅ እንዲሁም ደብዳቤ በቂ መሆኑን ገልጸው፤ ማንኛውም የመንግሥት ተቋማት የመተባበር ግዴታ እንዳለባቸው በዐዋጁ ላይ መቀመጡን ዶክተር አበራ ገልጸዋል።
የራጮች ትምህርት በሚሰጥባቸው ቀሪ ጊዜያት የፀጥታ አካላትም ሆኑ የባለድርሻ አካላት ትብብር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ከማህበራዊ ትስስር ገጹ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም